
ባሕር ዳር: ግንቦት 30/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የሲዳማ ክልል ርእሰ መሥተዳድር ደስታ ሌዳሞ እና የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ምክትል ርእሰ መሥተዳድር ተስፋየ ይገዙ በባሕር ዳር ከተማ ውስጥ የሚገነቡ መሠረተ ልማቶችን ተዘዋውረው ጎብኝተዋል። መሪዎቹ ከተመለከቷቸው ልማቶች መካከል የባሕር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም፣ ጣና ማሪና ዘመናዊ መዝናኛ፣ ዲፖ አረንጓዴ ልማት እና ከልደታ እስከ አየር መንገድ የሚገነባው ዘመናዊ የአስፓልት መንገድ ይገኙበታል።
ርእሰ መሥተዳድር ደስታ ሌዳሞ ወደ የሀዋሳ ከተማ አምሳያ ወደኾነችው ባሕር ዳር ከተማ ሲገቡ በተደረገላቸው አቀባበል መደሰታቸውን ገልጸው ምሥጋና አቅርበዋል። የአማራ ክልል ሕዝብ ሰላም ወዳድ፣ አኩሪ ባሕል እና ታሪክም ያለው ነው፤ ወደ ባሕር ዳር ስመጣ ደስ እያለኝ ነው የመጣሁት ብለዋል።
“ባሕር ዳር የሰላም ወዳድ ሕዝብ ከተማ ናት፤ ሰላሟ ተጠብቆ ትላልቅ የሕዝብ ልማቶች እየተከናወኑ በመመልከቴ ተደስቻለሁ” ሲሉም ገልጸዋል።
ርእሰ መሥተዳድሩ ባሕር ዳር ከተማ ውስጥ የሚገነቡ ትላልቅ ልማቶች አማራ ክልል ላይ ለሀገርም እድገት ትልቅ አበርክቶ ያላቸው ሥራዎች እየተከናወኑ ለመኾኑ ማሳያ ነው ብለዋል። በተለይም በጣና ሐይቅ ዳርቻ የሚሠሩ የቱሪዝም መሠረተ ልማቶች የሚያስደስቱ ናቸው ብለዋል። እንዲህ አይነት ትላልቅ ልማቶች ተጠናክረው ከቀጠሉ አካባቢው ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ የቱሪዝም መዳረሻ እንደሚኾንም ጠቁመዋል።
“ክልሉ ግጭት ውስጥ ገብቶ እንደነበር እናውቃለን፤ አሁን ላይ ግን አንጻራዊ ሰላም ሰፍኖበት ተመልክቻለሁ፤ ይህም ለልማት ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል” ብለዋል። አካባቢው የከፋ የሰላም ችግር እንዳለበት ከሩቅ ኾነው የሚያናፍሱ አሉ፤ ቀርበን እና በአካል ተገኝተን ስናየው ግን ሰላማዊ እና ልማቶችም የሚካሄዱበት ኾኖ አግኝተነዋል ነው ያሉት።
ርእሰ መሥተዳድሩ የተመለከቷቸው የልማት ሥራዎች ሕዝብን ተጠቃሚ የሚያደርጉ፤ በሥራ ሀገርን መለወጥ እንደሚቻልም ማሳያ የኾኑ ናቸው ሲሉ ገልጸዋል። ባሕር ዳር ከተማ ውስጥ ከሚሠሩ ልማቶች ተሞክሮ ወስደን በሀዋሳም ለመተግበር እንሠራለን ሲሉም ተናግረዋል። ክልሉ በተፈጥሮ ሃብት የታደለ ነው፤ ሕዝቡ ለሥራ ታታሪ ነው፤ የልማት ሥራዎችም እየተከናወኑ ነው፤ ይህንን አጠናክሮ ለመቀጠል ዘላቂ ሰላምን ማስፈን ያስፈልጋል ብለዋል።
“ሕዝብ ለሕዝብ እጅ ለእጅ ተያይዘን በጋራ በመቆም ለሀገራችን እድገት እንሠራለን፣ የሚከፋፍለንን ጉዳይ ወደኃላ በመተው ሀገራችንን ማሳደግ አለብን” ሲሉም መልእክት አስተላልፈዋል። የሚሠሩ የተለያዩ መሠረተ ልማቶችን ያስጎበኙት የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው በባሕር ዳር ከተማ ውስጥ ከአካባቢው ሕዝብም አልፎ እንደ ሀገር አስፈላጊ የኾኑ ልማቶች እየተሠሩ መኾኑን ገልጸዋል።
ጉብኝት ያደረጉ ከፍተኛ መሪዎች በልማት ሥራዎች መደሰታቸውንም ተናግረዋል። መሪዎቹ ባሕር ዳር ለኢትዮጵያ ትልቅ ተሥፋ፤ ኢትዮጵያ ከአማራ ክልል የምትፈልገውን የምትሰጥ ከተማ መኾኗን ያረጋገጡበትን ጉብኝት አድርገዋል ነው ያሉት ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው። ባሕር ዳር እና ሀዋሳ ሁለቱም በተፈጥሮ ውበት የታደሉ ናቸው፤ አንዱ የሌላውን ልምድ በመለዋወጥ እና በጋራ በመሥራት ለሕዝብ እና ለሀገር እድገት የሚበጁ ልማቶችን እናከናውናለን ሲሉም አቶ ጎሹ ተናግረዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!