
ባሕር ዳር: ግንቦት 30/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር መሐመድ እድሪስ ከኤስኢኤስ ሲንየር ማኔጅመንት ጋር ተወያይተዋል።
የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር መሐመድ እድሪስ ከኤስኢኤስ የሳተላይት አቅራቢ ድርጅት ሲንየር ማኔጅመንት ጋር ካምፓኒው አገልግሎቱን በቀጣይነት በጥራት በሚሰጥበት እና በባለሥልጣኑ የሪጉላቶሪ ሥራዎች ዙሪያ በሉግዘምበርግ በሚገኘው የካምፓኒው ዋና መስሪያ ቤት ተገኝተው ምክክር አድርገዋል።
በውይይቱም በኤስኢኤስ በኩል የአገልግሎት ጥራት እና ቀጣይነትን ወደፊት ለማሻሻል ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ መኾኑ ተገልጿል። በአሁኑ ጊዜ አገልግሎት እየሰጠ ያለውን የሳተላይት የአገልግሎትም ጊዜው ሲጠናቀቅ ያለምንም የአገልግሎት መቆራረጥ ለመተካት ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ መኾኑ ተገልጿል።
ካምፓኒው አገልግሎት እየሰጠ የሚገኘው በባለሥልጣኑ ሕጋዊ ዕውቅና ላላቸው መገናኛ ብዙኃን እንደሆነ እና በቀጣይም በዚሁ መንገድ ብቻ የሚያስተናግድ መኾኑን በውይይቱ ወቅት አሳውቋል። የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር መሐመድ እድሪስ በካምፓኒው በኩል ባለሥልጣኑ ተልዕኮውን እንዲወጣ እየተደረገ ላለው የሥራ ትብብር ምሥጋና አቅርበዋል።
ዋና ዳይሬክተሩ ካምፓኒው ከደንበኞቹ ጋር ፊት ለፊት የሚያደርገውን ውይይት አጠናክሮ እንዲቀጥል እና ለሀገር የኮርፓሬት ማኅበራዊ ኃላፊነት መገለጫ የሚኾኑ ሥራዎችን እንዲሠራ መጠየቃቸውን ከባለሥልጣኑ የማኅበራዊ ትስስር ገጽ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!