በአሜሪካ የኢትዮጵያ ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር ከአሜሪካ ምክር ቤት አባላት ጋር ተወያዩ።

20

ባሕር ዳር: ግንቦት 30/2016 ዓ.ም (አሚኮ)በአሜሪካ የኢትዮጵያ ልዩ መልዕክተኛ እና ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ስለሺ በቀለ (ዶ.ር.) የአሜሪካ ምክር ቤት አባል ከኾኑት ጄሪ ካርል እና ሮኒ ጃክሰን ጋር ተገናኝተው በኢትዮጵያ እና አሜሪካ ግንኙነት ዙሪያ ተወያይተዋል። በውይይታቸው ሁለቱ ሀገራት ከ120 ዓመታት በላይ የቆየ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት እንዳላቸው ተነስቷል።

ኢትዮጵያ ከአፍሪካ ሀገራት በሕዝብ ብዛት ሁለተኛ እና በፈጣን የኢኮኖሚ እድገት ላይ እንደምትገኝ ተገልጿል። በመኾኑም የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት ወደ ስትራቴጂካዊ አጋርነት ደረጃ ማሳደግ አስፈላጊ ስለመኾኑ ተነስቷል። በአፍሪካ ቀንድ ባለው የሰላም እና መረጋጋት ዙሪያም ውይይት ተደርጓል።

በተጨማሪም በኢትዮጵያ የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ መጽደቅ፣ ስለሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን፣ የሕዝብን ተጠቃሚነት ባረጋገጠ መልኩ በመንግሥት እየተተገበረ ያለው መጠነ ሰፊ የሪፎርም ሥራ፣ የባሕር በር ጉዳይ፣ አጎዋ ለኢትዮ-አሜሪካ ንግድ ግንኙነት ስላለው ፋይዳ ተነስቷል። በአሜሪካ የኢትዮጵያ ኢምባሲ በማኅበራዊ ትስስር ገጹ እንዳሰፈረው መረጃ ኢትዮጵያን ከአጎዋ እድል ተጠቃሚነት ማግለል በዜጎች ላይ እያደረሰ ያለው ጉዳት ከፍተኛ መኾኑ ተነስቷል። በተጨማሪም ኢትዮጵያ ውስጥ ኢንቨስት በሚያደርጉ የአሜሪካ ባለሃብቶች ላይም ተጽዕኖ እያሳደረ ስለመኾኑ አምባሳደሩ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleኢትዮጵያ ለደቡብ ሱዳን ዲፕሎማቶች ሥልጠና ሰጠች።
Next articleየኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር መሐመድ እድሪስ ከኤስኢኤስ ሲንየር ማኔጅመንት ጋር ተወያዩ።