
አዲስ አበባ: ግንቦት 30/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ነብዩ ተድላ በሰጡት ሳምንታዊ መግለጫ እንዳሉት የሳዑዲ አረቢያ የቢዝነስ ልዑካን ቡድን በኢትዮጵያ ጉብኝት አድርጎ ተመልሷል። ጉብኝቱ የቢዝነስ ዲፕሎማሲን ከማሳደግ ባለፈ ፖለቲካዊ እና የጸጥታ ትብብርን ያጠናክራል ነው ያሉት።
በግብርና፣ በማዕድን፣ በኃይል፣ በትራንስፖርት እንዲሁም በሎጀስቲክስ ላይ ምክክር በማድረግ የንግድ ስምምነት መደረጉንም አንስተዋል የሳዑዲ አረቢያ ባለሃብቶች ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት 260 ቢሊዮን ብር የሚያወጡ ፕሮጀክቶች ላይ በመሳተፍ ለ75 ሺህ ኢትዮጵያውያን የሥራ ዕድል ፈጥረዋል ብለዋል።
በቱርኪየ ኢስታንቡል ደግሞ የኢትዮ ተርኪየ የንግድ እና ኢንቨስትመንት ኤግዚቪሽን የተደረገ ሲኾን በዚህም የተርኪየ ባለሃብቶች በኢትዮጵያ እንዲሰማሩ ምክክር ማድረግ ተችሏል ነው ያሉት። አምባሳደር ነብዩ በደቡብ ኮሪያ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) መሪነት የተደረገው የዲፕሎማሲ እንቅስቃሴ ስኬታማ እንደነበር ያነሱ ሲኾን የአንድ ቢሊዮን ዶላር የቢዝነስ ማዕቀፍ ስምምነት ለዚሁ ማሳያ ነው ብለዋል።
ይህ የኢትዮጵያ ከፍተኛ ልዑክ በሲንጋፖር ጉብኝት ያደረገ ሲኾን በከተማ ልማት፣ በአረንጓዴ ኢኮኖሚ ግንባታ እና በከተማ ግብርና ልምድ መቅሰም የተቻለ ሲኾን የተለያዩ ስምነቶች መደረጋቸውንም አስገንዝበዋል። ለደቡብ ሱዳን ዲፕሎማቶች የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የሦስት ቀናት ሥልጠና ስለመሰጠቱም ተናግረዋል።
ለሀገሪቱ ዲፕሎማቶች የዕውቀት ሽግግር ከማድረግ ባለፈ የቀጣናውን ሁኔታ ቅርጽ ለማስያዝ ይጠቅማል ተብሏል። በሳምንቱ ሌሎች ዲፕሎማሲያዊ ክንውኖች እንደነበሩ በመግለጫቸው አብራርተዋል።
ዘጋቢ፦ አንዱዓለም መናን
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!