መንገድ በመዝጋት የሚመጣ መፍትሔ የለም ሲሉ የሃይማኖት መሪዎች እና የሀገር ሽማግሌዎች ተናገሩ።

59

ባሕር ዳር: ግንቦት 30/2016 ዓ.ም (አሚኮ)በደቡብ ጎንደር ዞን የወረታ ከተማ እና የፎገራ ወረዳ ባዘጋጁት “ሰላም ለሁሉም ሁሉም ለሰላም” በሚል መሪ መልዕክ በተዘጋጀው የምክክር መድረክ ተካሂዷል። በምክክር መድረኩ ላይ የተሳተፉ የሃይማኖት መሪዎች እና የሀገር ሽማግሌዎች “መንገድ በመዝጋት የሚመጣ መፍትሔ እና የሚረጋገጥ ነፃነት የለም” ብለዋል።

ሀገሪቱ ከገባችበት ቅርቃር ውስጥ መውጣት የምትችለው እና ሕዝቦቿም እንደ ሰማይ የራቃቸው ሰላም የሚመለሰው ከልብ በመነጨ ይቅር ባይነት ቁጭ ብሎ በመመካከር እንጂ ሆድ እና ጀርባ ኾኖ በመተያየት፣ በመገዳደል እንዲሁም መንገድ በመዝጋት አይደለም ነው ያሉት። የምክክር መድረኩ ተሳታፊ አባቶች ቋንቋችን ተደበላልቆብናል፣ ልናስታርቅ ስንወጣ መተማመን እና መግባባት አልቻልንም ብለዋል።

በወሊድ ምክንያት ወደ ባሕር ዳር ሪፈር የተፃፈላቸው እናቶች እና ሕጻናት መንገድ በመዘጋቱ እና የአምቡላንስ እንቅስቃሴ በመቆሙ ሕይዎታቸው እየተቀጠፈ ነው ሲሉ ያለውን አስከፊ ሁኔታ ገልጸውታል። የአማራን ሕዝብ የማይመጥን ጥቁር ታሪክ እየተፃፈ እንደኾነም አስረድተዋል። የይቅር ባይነት መንፈስ ሊኖር ይገባል ያሉት ተወያዮቹ የሰላም ውይይት እንዲኖር መንግሥትም ጥረት ማድረጉን እንዲቀጥል አሳስበዋል።

ለውይይት ዝግጁነቱ ካለ በጫካ ውስጥ የገቡትን ወንድሞች እጃቸው ለልማት፣ አንደበታቸው ለሰላም እና ልቦናቸው ለይቅርታ እንዲከፈት ለማድረግ ጥረት እንደሚያደርጉ ተናግረዋል። የወረታ ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ እሸቱ ሞላ እና የፎገራ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ እንድርያስ ማሩ መንግሥት ለሰላም የሚጠበቅበትን ይወጣል፣ የተዘረጉ የሰላም እጆችም አልተመለሱም ነው ያሉት።

የሃይማኖት አባቶች እና ታዋቂ ሽማግሌዎች ካለባቸው ድርብ ኀላፊነት በመነሳት ያልተወጡት ድርሻ እንዳለ ገልጸዋል። ልጆቻቸውን በማስተማር የሰላም ጥሪው ተጠቃሚ እንዲኾኑ እንዲያደርጉም አሳስበዋል። የደቡብ ጎንደር ዞን ዋና አስተዳዳሪ ጥላሁን ደጀኔ “አስተዋይ ሰው በፊቱ የገጠመውን መከራ ሳይኾን በልቡ ያለውን ዓላማ በማሰብ ይጓዛል” ብለዋል።

ዋና አስተዳዳሪው የሰው ልጅ ከተፈጠረበት ዓላማ ውጭ የኾኑትን እና በጫካ የሚኖሩትን ወገኖች ለተፈጠሩበት ከፈጣሪ ጋር ኅብረት የመፍጠር ዓላማ እንዲመለሱ ማስቻል ከሃይማኖት አባቶች እና ከሀገር ሽማግሌዎች የሚጠበቅ ሥራ እንደኾነ አስገንዝበዋል። “ሰላምን ለማስፈን እና ነፃነትን ለመጎናፀፍ ከሰዎች የምንጠብቀው ሳይኾን ከራሳችን መዳፍ የምናመርተው ሃብት ነው” ብለዋል።

ስለሰላም ሳይታክቱ መሥራት እንደሚጠበቅም አስገንዝበዋል። “የፖለቲካ አጀንዳ፣ አቋም እና ፖሊሲ አለኝ ይህንንም ዳር የሚያደርስ ወካይ አለኝ ብሎ ለሚቀርብ ማንኛውም የታጠቀ አካል ለሰላም እና ለድርድር የመንግሥታቸው በር ክፍት መኾኑን አሳስበዋል። እንደ ደቡብ ጎንደር ዞን የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን መምሪያ መረጃ የምክክር መድረኩ ተሳታፊዎች ከመገዳደል እና ከከፋፋይ አስተሳሰብ መውጣት እንደሚገባም አብራርተዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ርእሰ መሥተዳድር ጎንደር ከተማ ገቡ።
Next articleየአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም አረንጓዴ ልማት ያለውን ፋይዳ የተገነዘበ ማኅበረሰብ መፍጠር ያስፈልጋል።