የሳንባ ምች ምንድን ነው?

45

ባሕር ዳር: ግንቦት 30/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የሳንባ ምች በቫይረስ ወይንም በባክቴሪያ ምክንያት የሚመጣ የሳንባ ኢንፌክሽን ነው። በሽታው ማንኛውንም ሰው የሚያጠቃ ቢኾንም እድሜያቸው 65 እና ከዚያ በላይ የኾኑ አዋቂዎች እና ከ2 ዓመት በታች የኾኑ ህጻናት፣ የጤና እክል ያለባቸው ሰዎች እና የሚያጨሱ ሰዎች በከፍተኛ ሁኔታ ተጋላጭ ተደርገው ተቀምጠዋል።

በጥበበ ግዮን አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የጽኑ ሕሙማን ክፍል ዳይሬክተር ዶክተር አበበ ሹመት የሳንባ ምች በበሽታ አምጭ ተዋህስያን ምክንያት የሳንባ መቆጣት ወይንም መታወክ ሲከሰት የሚፈጠር ሕመም መኾኑን ገልጸዋል። ሕመሙ በአብዛኛው በባክቴሪያ የሚመጣ ቢኾንም ቫይረስም ሌላኛው አጋላጭ መንስዔ ነው። በሽታው በተዋህስያን አማካኝነት ከሚመጡ በሽታዎች መካከል ከፍተኛውን ቦታ እንደሚይዝም ገልጸዋል።

ህጻናት የበሽታ መከላከል አቅማቸው ያልዳበረ እና የበሽታው አጋላጭ ወደ ሰውነታቸው የመግባት አቅሙ ከፍተኛ በመኾኑ ይበልጥ ተጋላጭ መኾናቸውንም ነው ዶክተር አበበ የገለጹት። የሳንባ ምች የከንፈር እና ጥፍር ሰማያዊ መኾን፣ ድብርት፣ ፈሳሽ ያለው ሳል፣ ትኩሳት፣ ከባድ ላብ፣ የምግብ ፍላጎት ማጣት፣ ከፍተኛ ድካም፣ ቶሎ ቶሎ መተንፈስ፣ ፈጣን የልብ ምት፣ መንቀጥቀጥ ወይም ብርድ ብርድ ማለት ምልክቶቹ ናቸው።

እንደ ሐኪም አበበ ገለጻ የደረት ሕመም ወይም ውጋት፣ በተለይም በእንቅስቃሴ ወቅት እየተባባሰ የሚሄድ የትንፋሽ ማጠር፣ ራስ ምታት፣ የጡንቻ ሕመም እና ድካምም ሌሎች የሳንባ ሕመም ምልክቶች ናቸው፡፡ የሳንባ ምችን የተለያዩ ናሙናዎችን በመውሰድ እና በራጅ በሚደረግ ምርመራ መለየት እንደሚቻልም ዶክተር አበበ ገልጸዋል። በሽታው ከተለየ በኋላ እንደ ሕመሙ ዓይነት እና ደረጃ በተለያየ መንገድ ሕክምናው ይሰጣል።

በሽታው ከተገኘ በኋላም መድኃኒት ሳያቋርጡ መውሰድ፣ በአግባቡ ምግብ መመገብ፣ ፈሳሽ ነገሮችን በበቂ መውሰድ፣ እረፍት ማድረግ፣ ራስ ምታትን መቆጣጠር እንዲሁም የኦክስጅን ሕክምና መውሰድ በሽታው እንዳይባባስ እና ሌሎች ተጓዳኝ የጤና እክሎችን እንዳያስከትል ይረዳል፡፡
ዶክተር አበበ እንደሚሉት ንጽሕና መጠበቅ እና ከህሙማን ጋር ንክኪ ሲኖር የአፍ እና አፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል (ማስክ) ማድረግም በሽታውን ለመከላከል ያስችላል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበክልሉ እየተገነቡ የሚገኙ የኤሌክተሪክ ኃይል ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው ጊዜ እንዲጠናቀቁ ልዩ ክትትል እየተደረገ ነው።
Next articleየሲዳማ ክልል ርእሰ መሥተዳድር ደስታ ሌዳሞ ባሕር ዳር ገቡ።