በክልሉ እየተገነቡ የሚገኙ የኤሌክተሪክ ኃይል ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው ጊዜ እንዲጠናቀቁ ልዩ ክትትል እየተደረገ ነው።

18

ባሕር ዳር: ግንቦት 30/2016 ዓ.ም (አሚኮ)በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማእረግ የገጠር ዘርፍ አስተባባሪ እና የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ኅላፊ ድረስ ሳህሉ (ዶ.ር.)፣ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የንግድና ቱሪዝም ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰበሳቢ አሳቻለ አላምሬ፣ የመከላከያ ሠራዊት ከፍተኛ መኮንኖች፣ የክልሉ እና የምስራቅ ጎጃም ዞን የሥራ ኅላፊዎች የደጀን ኤሌክትሪክ ኃይል ማከፋፈያ ጣቢያ የግንባታ ሂደትን ተመልክተዋል።

የደጀን የኤሌክትሪክ ኃይል ማከፋፈያ ጣቢያ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል በመደበው 285 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት በ2013 ዓ.ም ጀምሮ ግንባታው እየተከናወነ እንደነበር ይታወሳል። ግንባታው በግብዓት ችግር ምክንያት በተቀመጠው ጊዜ መጠናቀቅ አልቻለም ያሉት በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የደጀን የኤሌክትሪክ ኃይል ማከፋፈያ ጣቢያ ግንባታ ተቆጣጣሪ እና አማካሪ ግርማ ብርሃኑ ግንባታውን እስከ 2017 ዓ.ም መጀመሪያ ለማጠናቀቅ እየሠራን ነው ብለዋል።

የደጀን የኤሌክትሪክ ኃይል ማከፋፈያ ጣቢያ የግንባታ ሂደትን የተመለከቱት በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማእረግ የገጠር ዘርፍ አስተባባሪ እና የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ኅላፊ ድረስ ሳህሉ (ዶ.ር.) በክልሉ እየተገነቡ የሚገኙ የኤሌክተሪክ ኃይል ማከፋፈያ ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው ጊዜ እንዲጠናቀቁ ልዩ ክትትል እየተደረገ ነው ብለዋል።

ዶክተር ድረስ ሳህሉ በክልሉ በተከሰተው የፀጥታ ችግር ምክንያት የተጓተቱ ፕሮጀክቶች መጠናቀቅ እንዲችሉ የክልሉ ሕዝብ ፕሮጀክቶችን እንዲጠብቅ እና ሰላም እንዲረጋገጥ የድርሻውን እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል። በዞኑ የሚገኙ የልማት ፕሮጀክቶችን የጎበኙት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል እና የንግድ እና ቱሪዝም ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰበሳቢ አሳቻለ አላምሬ የደጀን ኤሌክትሪክ ኃይል ማከፋፈያ ጣቢያ የአካባቢውን ሕዝብ የኃይል አቅርቦት ችግር የሚፈታ እና ኢንቨስትመንትን የሚያነቃቃ ነው ብለዋል።

አቶ አስቻለ ሕግ እና ሥርዓት ባለመከበሩ ሰብዓዊ እና ቁሳዊ ጉዳት መድረሱን አስታውሰው አለመግባባቶች በንግግር እንዲፈቱ ሁሉም ለሰላም ቅድሚያ እንዲሰጥ አሳስበዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ከሳዑዲ አረቢያ ከፍተኛ የኢንቨስትመንት ተወካዮች ልዑክ ጋር ተወያዩ።
Next articleየሳንባ ምች ምንድን ነው?