
ባሕር ዳር: ግንቦት 29/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ሕዝብ ሙዚየም ታሪክ በወጉ የሚቀመጥበት እና የጎብኝዎች ማዕከል እንዲኾን ታስቦ እየተሠራ መኾኑን በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የከተማ ዘርፍ ኀላፊ እና የከተማ እና መሠረተ ልማት ቢሮ ኀላፊ አሕመዲን ሙሐመድ (ዶ.ር) ገልጸዋል።
ዶክተር አሕመዲን በባሕር ዳር ከተማ የሚገነባውን የአማራ ሕዝብ ሙዚየም የግንባታ ሂደት ተመልክተዋል።
ከዚህም በተጨማሪ የአማራ ሕዝብ ዝክረ ታሪክ ማዕከልን ጎብኝተዋል።
የአማራ ክልል ባሕል እና ቱሪዝም ቢሮ ኀላፊ መልካሙ ጸጋየ እና ሌሎችም የባሕል እና ቱሪዝም መሪዎች በምልከታው ተሳትፈዋል።
ዶክተር አሕመዲን ከሁሉም ባሕል እና ቱሪዝም መሪዎች ጋር ውይይት ማድረጋቸውን ገልጸዋል።
የውይይቱ ዓላማ በክልሉ ያለውን እምቅ ቅርስ እና ባሕል ወደ ቱሪዝም ኢኮኖሚ በማስገባት ሕዝብን ተጠቃሚ ለማድረግ ያለመ ነው።
በዚህም መሠረት ዛሬ በ1 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር ወጭ የሚሠራውን የአማራ ሕዝብ ሙዚየም ግንባታ ተመልክተዋል።
ከዚህ በፊት ስለክልሉ ሕዝብ ባሕል፣ ቋንቋ እና እሴቶች ጥናት እና ምርምር የሚደረግበት ኹነኛ ክልላዊ ተቋም እንዳልነበረ ዶክተር አሕመዲን ጠቅሰዋል።
ኢትዮጵያ በጋራ የተገነባች ሀገር ናት፤ ከሌሎች ሕዝቦች ጋር በጥብቅ ቁርኝት ለመኖር የሚያስችሉ እሴቶችን የበለጠ ማሳደግ ያስፈልጋል፤ እየተሠራ ያለው ሙዚየምም የአማራ ክልል ሕዝብን መልካም እሴቶች ለመጠበቅ እና ለማሳደግ ያግዛል ነው ያሉት።
ዶክተር አሕመዲን “ሙዚየሙ ያለፉ ታሪኮቻችንን የሚያሳዩ ሥራዎች በወጉ እንዲቀመጡበት፣ የጎብኝዎችም ማዕከል እንዲኾን ታስቦ እየተሠራ ነው” ሲሉ ተናግረዋል።
ግንባታው መሻሻል ያለበት የዲዛይን ሥራ እየተሻሻለ ይሠራል፤ በአጭር ጊዜም ይጠናቀቃል ብለዋል።
ቀደም ሲል የተሠራው የአማራ ሕዝብ ዝክረ ታሪክ ማዕከልም በርካታ ታሪክ እና እሴቶችን በውስጥ የያዘ፣ ጎብኝዎችን በማስተናገድ ገቢ እያመነጨ እንደሚገኝም ገልጸዋል።
ማዕከሉ የሕዝቡን ታሪካዊ ጉዞ፣ አለባበስ፣ መገልገያ ቁሳቁሶች እና በርካታ ባሕል እና እሴቶችን የሚያንጸባርቁ ጉዳዮችን መያዙንም ገልጸዋል።
ማዕከሉን በአግባቡ በመያዝ በአቅሙ ልክ የኾነ ገቢ እንዲያመነጭ ማድረግ እንደሚገባም አሳስበዋል።
ማዕከሉን በማልማት፣ በማስፋት እና ቴክኖሎጂን በመጠቀም የበለጠ በማስዋብ የባሕር ዳር ከተማ ምርጡ የጎብኝዎች መዳረሻ እንዲኾን አቅጣጫ ስለመቀመጡም ተናግረዋል።
ይህንን ለመሥራት ከዲዛይን ጀምሮ በርካታ ወጪ እንደሚጠይቅ ገልጸው በዙሪያው ካሉ ባለይዞታዎች ጋር በመመካከር፤ የበለጠ ተጠቃሚ የሚኾኑበትን መንገድም በማመቻቸት ቦታውን እስከ አዲሱ ድልድይ ድረስ አስተሳስሮ ለማልማት እየተሠራ ነው ብለዋል።
የአማራ ክልል ባሕልና ቱሪዝም ቢሮ ኀላፊ መልካሙ ጸጋየ እንደገለጹት የዛሬው ጉብኝት ዋና ዓላማ የአማራ ሕዝብ ሙዚየም የግንባታ ሂደት ያለበትን ሁኔታ ለመመልከት፣ ለመገምገም እና ችግሮች ካሉም ለይቶ በመፍታት የቀጣይ አቅጣጫ ለማስቀመጥ ነው።
ፕሮጀክቱ በሲሚንቶ አቅርቦት እና የግንባታ እቃዎችን በማጓጓዝ ረገድ በገጠመው ችግር ምክንያት መጓተት እንደገጠመውም ገልጸዋል።
ፕሮጀክቱ አሁን ላይ በጥሩ የግንባታ ሂደት ላይ እንዳለም ጠቅሰዋል።
ክልሉ ግዙፍ ቢኾንም ራሱን የቻለ ሙዚየም የለውም ነበር፤ አሁን ግን የራሱ የኾነ ሙዚየም እንዲኖረው ታስቦ በትኩረት እየተሠራ ነው ብለዋል።
የተጀመረው የሙዚየም ግንባታ ሲጠናቀቅ የሕዝቡ ባሕል፣ ቋንቋ፣ እና እሴቶችን የተመለከተ ጥናት እና ምርምሮችን ለማካሄድ ያገለግላል ብለዋል።
አማራ ክልል በርካታ ዓለም አቀፍ ቅርሶች ጭምር ያሉበት፣ የቱባ ባሕል፣ ወግ እና እሴት ባለቤት ነው፤ እነዚህን በተደራጀ መንገድ ለማስተዋወቅ የተጀመረው ሙዚየም ከፍተኛ ፋይዳ እንደሚኖረውም አብራርተዋል።
የግንባታ ሥራው ሳይቆራረጥ እንዲከናወን እና በተያዘለት ጊዜ እንዲጠናቀቅ በትኩረት እንደሚሠራም ገልጸዋል።
ሙዚየሙን ከአማራ ሕዝብ ዝክረ ታሪክ ማዕከል እና ከአዲሱ የዓባይ ወንዝ ድልድይ ጋር በማስተሳሰር ሲለማ የቱሪዝም መነቃቃትን እንደሚፈጥርም አብራርተዋል።
የባሕል እና ቱሪዝም ቢሮው ምክትል ኀላፊ አየለ አናውጤ (ዶ.ር) የሕዝቡን አበርክቶ የሚመጥን እና የተደራጀ ሙዚየም አቋቁሞ ትውልዱን ከማስተማር፣ ባሕል እና ወጉንም ወደሌላ ትውልድ ከማስተላለፍ አኳያ ክፍተት እንደነበር ጠቁመዋል።
አሁን ላይ ግን የክልሉ መንግሥት ለሙዚየም ግንባታው ከፍተኛ ድጋፍ እያደረገ ስለመኾኑ ገልጸዋል።
ግንባታው በአማራ ሕንጻ ሥራዎች ድርጅት ተቋራጭነት እየተከናወነ እንደሚገኝ እና ቢሮው ከፍተኛ ክትትል እያደረገ መኾኑን ተናግረዋል።
ዶክተር አየለ የተፈጥሮ ውበት በታደለ ቦታ ላይ ያረፈውን የአማራ ሕዝብ ዝክረ ታሪክ ማዕከል ከዓባይ ወንዝ ጋር አስተሳስሮ ለማልማት የዲዛይን ሥራ መሠራቱን ገልጸዋል።
በአማራ ሕንጻ ሥራዎች ድርጅት ተቋራጭነት የሚገነባው የአማራ ሕዝብ ሙዚየም ግንባታ ፕሮጀክት ሥራ አሥኪያጅ አንድነት ቦጋለ ግንባታው የተጀመረው ሕዳር 17/2016 ዓ.ም መኾኑን ገልጸዋል።
ለሥራው የተመደበለት ጊዜ አራት ዓመት ሲኾን አሁን ላይ አፈጻጸሙ 18 ነጥብ 8 ላይ መድረሱንም ጠቁመዋል።
አቶ አንድነት አፈጻጸሙ የተወሰነ መዘግየት እንደገጠመው ገልጸዋል። በዚህ ወቅት 23 በመቶ መድረስ እንደነበረበትም ጠቁመዋል።
አሁን ላይ በትኩረት እየተሠራ ነው፤ 2019 ዓ.ም አጋማሽ አካባቢ ይጠናቀቃል ተብሎም ይጠበቃል ብለዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!