ለዓመታት የዘገየው የደብረ ማርቆስ ጠቅላላ ሆስፒታል ግንባታ በፍጥነት ለማጠናቀቅ እየተሠራ መኾኑን የአማራ ክልል ጤና ቢሮ አስታወቀ።

67

ደብረ ማርቆስ: ግንቦት 29/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማእረግ የገጠር ዘርፍ አስተባባሪ እና የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ኀላፊ ድረስ ሳህሉን (ዶ.ር.) ጨምሮ የክልሉ እና የዞኑ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኀላፊዎች የሆስፒታሉን የግንባታ ሂደት ተመልክተዋል። 5 ሚሊዮን የሚጠጋ ሕዝብ ያገለግላል ተብሎ በ2009 ዓ.ም ግንባታው የተጀመረው የደብረ ማርቆስ ጠቅላላ ሆስፒታል በተለያዩ ምክንያቶች ግንባታው ሲጓተት መቆየቱ ይታወሳል።

የተቋረጠውን ሆስፒታል ግንባታ ለማስቀጠል የክልሉ መንግሥት በወሰደው እርምጃ ቀደም ሲል ግንባታውን ከያዘው የመቅደላ ኮንስትራክሽን ውል በማቋረጥ በ2015 መጨረሻ ለአዲስ ተቋራጭ ከተላለፈ ወዲህ ግንባታው በተሻለ ፍጥነት እየተከናወነ መኾኑን የአማራ ክልል ጤና ቢሮ ምክትል ኀላፊ መልካሙ ጌትነት ተናግረዋል።

የሆስፒታሉን የግንባታ ሂደት የተመለከቱት በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማእረግ የገጠር ዘርፍ አስተባባሪ እና የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ኀላፊ ድረስ ሳህሉ (ዶ.ር.) የደብረ ማርቆስ ጠቅላላ ሆስፒታልን ጨምሮ በፀጥታ እና ሌሎች ምክንያቶች የተጓተቱ የልማት ፕሮጀክቶችን በጊዜ ለማጠናቀቅ የክልሉ መንግሥት በልዩ ትኩረት እየሠራ ነው ብለዋል።

የሆስፒታሉን ግንባታ በ700 ቀናት አጠናቅቆ ለማስረከብ ውል የወሰደው የመንቆረር ኮንስትራክሽን ግንባታው በ2012 ሲቋረጥ ከነበረበት 39 በመቶ ወደ 64 በመቶ ማድረሱን የጠቅላላ ሆስፒታሉ ግንባታ መሐንዲስ ኢንጅነር አስናቀ ደሴ ተናግረዋል። ኢንጅነር አስናቀ ግንባታውን በተወሰደው ውል መሠረት በጊዜው በማጠናቀቅ ለሕዝቡ አገልግሎት እንዲሰጥ በትጋት እየሠሩ መኾናቸውንም ተናግረዋል።

የምስራቅ ጎጀም ዞን ዋና አስተዳዳሪ ኑርልኝ ብርሃኑ በዞኑ አንጻራዊ ሰላም መምጣቱን ተከትሎ በቀጣይ ወራት በዞኑ ውስጥ የጎጃም ባሕል ግንባታን ጨምሮ የተጓተቱ ሌሎች የልማት ፕሮጀክቶችን በፍጥነት ለማከናወን አስተዳደሩ በትኩረት እየሠራ ነው ብለዋል። የክልሉ እና የዞኑ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኀላፊዎች በዞኑ እየተከናወኑ የሚገኙ የልማት ሥራዎችን ተዘዋውረው ተመልክተዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“የራያ እጣፋንታው እና አምሳያው አማራ ነው” ዛዲግ አብርሃ
Next articleየአማራ ሕዝብ ሙዚየም ታሪክ በወጉ የሚቀመጥበት እና የጎብኝዎች ማዕከል እንዲኾን ታስቦ እየተሠራ ነው።