“ከሳጥኑ እንውጣ” – አሮጌው የፖለቲካ ካፖርት ይውለቅ

32

ባሕር ዳር: ግንቦት 29/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ነፍሳቸው በሰላም ትረፍና ዕውቁ ኢትዮጵያዊ የሥነ ጽሑፍ ሰው ፀጋየ ገብረመድኅን “ሞክረናቸው ካልተሳኩት በርካታ ጉዳዮች ይልቅ፤ ፍጹም ያልሞከርናቸው ትንሽ ነገሮች ይበልጥ ያስቆጩናል” ይሉ ነበር፡፡ እውነት ነው! የሰው ልጅ በባሕሪው ጥሮ እና ግሮ ካልተሳኩለት አያሌ የመለወጥ ሙከራዎቹ ይልቅ፤ በዋዛ እና በፈዛዛ፣ በስንፈት እና በፍርሃት፣ በአጉል ስሜት እና አርቆ ባለማየት ጭራሽ ሳይፈትሻቸው እንደ ዋዛ ያለፉ ትንንሽ የመፍትሔ መንገዶች ይበልጥ ያስቆጩታል፡፡

እንዳለመታደል ኾኖ በኢትዮጵያ የፖለቲካ ሰማይ ስር ከላይ ካነሳነው የሰው ልጅ ተፈጥሯዊ ባሕሪ በእጅጉ በራቀ መልኩ ኢትዮጵያን እና ኢትዮጵያዊነትን ደግመው ደጋግመው አፈር ድሜ ካስጋጡት ተመሳሳይ አዙሪቶች ጋር ባሉበት መርገጥ ዛሬም ድረስ የታሪካችን አንድ አካል ኾኖ ቀጥሏል፡፡ ላለመቆጨት ሲባል እንኳን ያልሞከሯቸውን ትንሽ እና ቀናዒ ነገሮች አደብ ገዝቶ መሞከር እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ከሰማይም ርቆን ቆይቷል፡፡ ለመለወጥ የምንዳዳ እና መፃዒውን በውል የማንረዳ እስክንመስል ድረስ የፖለቲካ ባሕላችን ችኮ መንቻካ፣ ድግግሞሽ የበዛበት፣ አሰልቺ እና መራር ዋጋ የሚያስከፍል ኾኖ ይስተዋላል፡፡

ባለተሰጥኦ ጸሐፊው በዕውቀቱ ስዩም ሩቅ ምሥራቃዊውን የሩቅ ዘመን ባለቅኔ ዑመር ካያምን ዋቢ አድርጎ “በወጣትነቴ የእድሜየ አፍላ ጀምበር፤ የሊቅ የጣዲቁን ሁለገብ ሃተታ አዘወትር ነበር፡፡ ታዲያ ምን አተረፍኩ! ተመልሸ ወጣሁ በገባሁበት በር” ይለናል፡፡ ነፍጥ አንግበው እና ነጻ አውጭ ነን ብለው ገብተው በዘመን ነጻ አውጪዎች እና አንጋቾች እንዳይሆን ኾነው የተሸኙት እልፍ ናቸው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ በመጡበት መንገድ የተሸኙት፤ በወጡበት መሰላል የወረዱት በእጅጉ ይበዛሉ፡፡

ለኢትዮጵያ የሀገረ መንግሥቷ ወጌሻ እና የልዕለ ኃያልነቷ መነሻ ነን ብለው በኃይል ገብተው ነገር ግን ስብራቶቿን አበራክተው እና ችግሮቿን አከማችተው በኃይል የተገረሰሱት ቁሞ ቆጣሪ ከተገኘ የትየለሌ ናቸው፡፡ በተቃውሞ ገብቶ በተቃውሞ መውጣት፤ በሴራ ተገንብቶ በሴራ መናድ፤ በአፈሙዝ ወጥቶ በአፈሙዝ መውረድ፤ መንበረ ሥልጣን በኃይል ተቆናጥጦ ከመንበረ ሥልጣን በኃል መፍረጥ ቢያንስ ያለፉት ስድስት አስርት ዓመታት የሀገሪቷ የሀገረ መንግሥት ግንባታ ሂደት እውነታ ነው፤ ጠባሳው የማይፋቅ ታሪክ ነው፡፡

ለረጂም ዘመናት ለሀገር ይበጃል፤ ትውልድ ያደረጃል የተባለላቸው የሀገረ መንግሥት ግንባታ መንገዶቻችን ተመሳሳይ አዙሪት ውስጥ የሚሽከረከሩ ድግግሞሽ ናቸው፡፡ ይበልጥ የሚያሳዝነው ደግሞ ተደጋግሞ የሚበዛባቸው የለውጥ መንገዶቻችን ብቻ ሳይኾኑ መንገደኞቹም ተመሳሳዮች እና አንድ መኾናቸው ነው፡፡ የተፈጥሮ ሕግ መጥቶ ገሸሽ እስካላደረጋቸው ድረስ መንገዶቻችን ብቻ ሳይኾኑ መንገደኞቹም በእጣት የሚቆጠሩ ውስን ልሂቃን ናቸው፡፡

ይበልጡን የሚገርመው ደግሞ እነዚህ ልሂቃን እስትንፋሳቸው ካልኾነም ሌጋሲያቸው፤ አሻራቸው ካለበለዚያ ደግሞ መንፈሳቸው አሁንም ድረስ የፖለቲካ አየሩን ይበክላል፡፡ በየታሪክ እጥፋቱ እና በየለውጥ ክስተቱ መካከል ሁሉ “አዲሲቷ” የሚባልላት ኢትዮጵያ ብዙዎቹ ተዋናዮቿም ዘዋሪዎቿም አዛውንቶች ናቸው፡፡ እዚህ ላይ አንባቢ በውል መገንዘብ ያለበት ሃቅ ቢኖር በቀደመው የኢትዮጵያ ሀገረ መንግሥት ምሥረታ ታሪክ ድርሻ የነበራቸው ሁሉ በመጻዒው የሀገረ መንግሥት ምስረታ ሂደት ፍጹም አበርክቶ ሊኖራቸው አይገባም ማለት አይደለም፡፡ ቢያንስ አሰላለፋቸውን ይቀይሩ እንጂ፡፡ ሚናቸው ሊቀየር እና እሳቤያቸው ሊሻሻል ተፈጥሯዊ ግዴታ አለበት፡፡

በነገዋ ኢትዮጵያ መፃዒ እጣ ፋንታ ውስጥ ቀንበር ተሸካሚ ትውልድ መፍጠር ለነገ የማይባል የቤት ሥራ ነው፡፡ የኢትዮጵያን ችግሮች በስክነት፤ መፍትሔዎቿን በብስለት ማየት ለሚችል ሁሉ፤ ሀገሪቷ አዲስ የፖለቲካ ባሕል መገንባት በሚያስፈልግባት ጊዜ እና መንገድ ላይ ነች፡፡ በአዲስ የሀገረ መንግሥት ግንባታ ልምምድ ሂደት ውስጥ ደግሞ ቀደምቶቹ ከአድራጊ ፈጣሪነት ፈቀቅ ብለው መካሪ እና ዘካሪ ሊኾኑ ይገባል፡፡ ውጣ ውረዶቻቸውን ዘርዝረው፤ ትርፍ እና ኪሳራውን ቀምረው ከእኛ የሀገረ መንግሥት ግንባታ ረጂም ጉዞ የተረዳነው ይኽ ነው ማለት ይጠበቃል፡፡ ጉዟችንን አይታችሁ፣ መንገዶቻችን መርምራችሁ እና ዘመኑን ዋጅታችሁ ኢትዮጵያዊ ለዛ እና ወዘና ያለው ሀገረ መንግሥት በምክክር መሥርቱ፤ እኛ ከጎናችሁ ነን ማለትን ማውረስ ይጠበቃል፡፡

ጉዳዩን ፍጹም ወቀሳ እና ውለታ ቢስነት አድርጎ መመልከትም አይገባም፡፡ ጉዳዩ አዛውንቶቹ በኢትዮጵያ የሀገረ መንግሥት ጉዳይ “ሩጫችን ጨርሰናል” እንዲሉ ሳይኾን ነጮቹ እንደሚሉት “ፒስ ሜከር” ወይም “አሯሯጮች” እንዲኾኑ ነው፡፡ ጥያቄው የቀደመው የመሮጫ መም ወይም ትራክ ይቀየር ነው፡፡ በኃይል መተካካት፣ በግጭት መለካካት እና በሴራ መፈራረቅ በየዘመኑ ብቅ የሚለውን ትውልድ ያልበላው እዳ ከፋይ ከማድረግ የዘለለ ጠብ ያደረገው ለውጥ የለም፡፡ ያልተሞከረ የሩጫ መስመር አለ፤ መገዳደል፣ መታኮስ እና መወቃቀስ የሀገሪቷን የትናንት ቁስል አልሻረውም፤ ስብራቷን አልጠገነውምና ሌላ መንገድ ማየት ዘመኑን መዋጀት ተገቢ ነው፡፡

ኤፍሬም ማዴቦ 2013 ዓ.ም ላይ “ኢትዮጵያ እና ሕገ መንግሥታዊ ምርጫዎቿ” በሚል ርእስ ባሳተሙት እና የሀገሪቷን የምርጫ ሥርዓት፣ የመንግሥት መዋቅር እና ቅርጽ በስፋት በዳሰሱበት መጽሐፋቸው መግቢያ ላይ “በታላላቆቹ የኢትዮጵያ ሕግ መንግሥታዊ ጥያቄዎች ላይ ሕዝባዊ፣ ምሁራዊ እና አካባቢያዊ ምክክሮች አሁኑኑ መጀመር አለበት” ሲሉ ምክረ ሃሳብ ያቀርባሉ፡፡ ጥያቄው የብዙኀኑ ኢትዮጵያዊ አሳቢ እና ልሂቅ ጥያቄ እንደነበርም በተደጋጋሚ ሲስተጋባ ታዝበናል፡፡

ከላይ ያነሳናቸው ጸሐፊ በምክክሩ ሂደት ሁሉም ኢትዮጵያዊ ድርሻ ቢኖረውም የፖለቲካ ልሂቁ ድርሻ ግን ይልቃል ባይ ናቸው፡፡ አቶ ኤፍሬም በመግቢያቸው እንደሚሉት ሀገራት በጎም መጥፎም የምክክር ታሪክ እንዳላቸው ጠቅሰው ለምክክሩ ስኬት ቅንነት እና መረዳት ወሳኝ ነው ይላሉ፡፡ አያይዘውም ሀገራዊ ምክክሩ እና ውይይቱ በየትም ቦታ ሊኾን እና በየደረጃው ሊካሄድ እንደሚገባ ጠቁመው ነገር ግን የምክክሩ ፍጻሜ ኢትዮጵያ ውስጥ እና በኢትዮጵያዊያን ማለቅ ይኖርበታል ይላሉ፡፡ የውጭ ኃይል ያልነካው የማይቦካ የሚመስለን በርካቶች ስለኾንን የጸሐፊው ስጋትም እሱ ይመስለኛል፡፡

አሁን ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ተቋቁሞ የቅድመ ዝግጅት ምዕራፉን አጠናቅቆ ወደ ምክክሩ እየገባ ነው፡፡ አቶ ኤፍሬም ማዴቦ እና ሌሎችም እንደሚሉት ዛሬ ኢትዮጵያ እየመከረች ነው፡፡ ኢትዮጵያ በታሪኳ ፍጹም ባልሞከረችው አዲስ የሀገረ መንግሥት ግንባታ መንገድ ላይ ነች፡፡ ሀገራዊ ምክክሩ የፍትሕ ጉባኤ የፍቅር ሱባኤ፤ የይቅርታ ሶላት የመቀራረብ ስግደት የሚከወንበት ነው፡፡ ጉባኤውም ሱባኤውም፤ ሶላቱም ስግደቱም ንጹህ ልብ እና ፍጹም ትህትናን ይጠይቃሉ፡፡ ሀገራዊ ምክክሩም የሚፈልገው ይህንን ቅንነት ነው፡፡

በሕገ መንግሥት ዝግጅት ወቅት የገጠመው አይነት ጸጸት እና ቅሬታ እንዳይፈጠር ደግሞ ከሊቅ እስከ ደቂቅ፤ ከወጣት እስከ አዛውንት የሁሉም ኢትዮጵያዊ ተሳትፎ ዋጋው ታላቅ ነው፡፡ ቢያንስ እንኳን እስካለንበት ወቅት ድረስ ለስድስት አስርት ዓመታት የዘለቀው አሮጌ የፖለቲካ ባሕል ካፖርቱ በምክክር ይወልቅ ዘንድ መትጋት ግድ ይላል፡፡ ኢትዮጵያም በተደጋጋሚ ጊዜ ከሚጎበኛት ደም አፋሳሽ ግጭት ወጥታ የቀደመ የምክክር ባሕሏን ታድስ፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ከተረጂነት እንውጣ የሚል አብዮት መቀስቀስ አለብን” ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ
Next article“የራያ እጣፋንታው እና አምሳያው አማራ ነው” ዛዲግ አብርሃ