
ባሕር ዳር: ግንቦት 29/2016 ዓ.ም (አሚኮ)ተፈጥሯዊም ይሁን ሰው ሰራሽ አደጋ አይቀሬ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ አደጋን በራስ አቅም የማስተዳደር እና የመሸከም አቅምን ማጎልበት ይገባል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ “ከተረጂነት እንውጣ የሚል አብዮት መቀስቀስ አለብን” ብለዋል።
ዛሬ ባደረጉት የአደጋ ስጋት ሥራ አመራር ምክር ቤት መደበኛ ስብሰባ ላይም በአዲስ መልክ በፀደቀው የአደጋ ስጋት ሥራ አመራር ፖሊሲ መወያየታቸውንም በማኅበራዊ የትስስር ገጻቸው አጋርተዋል፡፡
በውይይቱ የ2016 በጀት ዓመት የአደጋ ስጋት ሥራ አመራር ዕቅድ አፈጻጸምን መገምገሙንም ጠቁመዋል፡፡የአደጋ ስጋት ሥራዎች በሙሉ አቅም ለመፈፀም የባሕል ልውጥ ያስፈልጋል ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ የባሕል ለውጥ ለማምጣት ደግሞ ልመናን የሚፀየፍ ትውልድን መፍጠር፣ የቆዬውን የመደጋገፍና የመረዳዳት ማኅበራዊ እሴት ማጠናከር እና በማጎልበት ራስን መቻል ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
በአድዋ ጊዜ የነበረንን የአርበኝነት ወኔ እና ተነሳሽነት ድኅነትን ለማሸነፍ መጠቀም ይኖርብናል ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ለዚህ ደግሞ እንደ ሀገር የጀመርናቸውን ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ ልማቶች ማፋጠን ወሳኝ ነው ብለዋል። ዋናው ጠላታችን የኾነውን ድኅነት እና ኋላቀርነትን ማሸነፍ ለነገ የማይባል ተግባር እንደኾነሞ ጠቁመዋል።
የአደጋ ስጋት ሥራ አመራር የአንድ ወገን ሥራ ብቻ አይደለም፡፡ ይልቁንስ ሁሉንም ባለድርሻ አካላት በጋራ አሳታፊ በማድረግ ሊሰራበት የሚገባ ጉዳይ ነው ብለዋል፡፡ በሌላ በኩል ይህንን ቅንጅታዊ አሰራር በቴክኖሎጂ በመደገፍ የመረጃ ጥራትን ማሳደግ ያስፈልጋል፡፡ ይህ ደግሞ ውሳኔዎችን በተገቢው መንገድ ለማሳለፍ በዕጅጉ ጠቃሚ ነው ብለዋል፡፡
በቀጣይም የማይመጥነንን የተረጂነት እና የጠባቂነት አስተሳሰብ ክብረ-ነክ፣ ነፃነትን የሚያሳጣ እና የሉዓላዊነት ሳንካ መኾኑን በመረዳት ከመሪ እስከ ዜጋ መግባባት በፍጠር የጀመርነውን አብዮት ለማስቀጠል ከስምምነት ላይ ደርሰናል ነው ያሉት፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!