
ባሕር ዳር: ግንቦት 29/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የወጣቶችን የዲጂታል ሥራ ፈጠራ ክህሎት በማጎልበት ዲጂታል ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ በልዩ ትኩረት እየተሠራ መኾኑን የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ (ዶ.ር) ተናግረዋል። የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ከአጋር አካላት ጋር በመተባበር በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ውስጥ ተግባራዊ የሚደረገውን ሀገር አቀፍ የክህሎት ሥልጠና ፕሮግራም በይፋ አስጀምሯል።
የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስትሩ በለጠ ሞላ (ዶ.ር) በአኹኑ ወቅት በሁሉም መስኮች ዲጂታል አሠራሮችን የመጠቀም ልምድ እየሰፋ መጥቷል ነው ያሉት፡፡ ይኽም ዲጂታል ኢትዮጵያን እውን ከማድረግ ባሻገር ኢኮኖሚያዊ ፋይዳው የጎላ መኾኑን ገልጸዋል። ከዚህ አኳያ ሚኒስቴሩ በተለይ የወጣቶችን የዲጂታል ሥራ ፈጠራ ክህሎት ለማስፋት የሚያስችሉ ተግባራትን እያከናወነ ስለመኾኑ አንስተዋል።
ሚኒስቴሩ ከሳፋሪኮም ኢትዮጵያ እና ከጃፓኑ ዓለም አቀፍ ትብብር (ጃይካ) ጋር የወጣቶችን የዲጂታል ሥራ ፈጠራ ክህሎትን ለማጎልበት የሚያስችል ስምምነት ማድረጉንም አስታውሰዋል፡፡ የስምምነቱ ዋነኛ ዓላማ ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ጋር በመተባበር በተለያዩ ዘርፎች የዲጂታል ክህሎት ሥልጠናዎችን መስጠት መኾኑንም አክለዋል።
በዚህም በመጀመሪያው ዙር በተመረጡ ስድስት ዩኒቨርሲቲዎች ለ10 ሺህ ዜጎች የዲጂታል ክህሎት ሥልጠና ይሰጣል ብለዋል። የክህሎት ሥልጠናው በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውስጥ የሚገኙ ተማሪዎችን ጨምሮ በአካባቢው ያሉና በተለያዩ የፈጠራ ሥራ መሰማራት የሚፈልጉ ዜጎችንም ተደራሽ የሚያደርግ ነው ብለዋል።
በቀጣይም ሥልጠናውን ወደ ሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች የማስፋት ሥራ እንደሚከናወን አረጋግጠዋል። የጃፓኑ ዓለም አቀፍ ትብብር(ጃይካ) የኢትዮጵያ ተወካይ ቺ ሺሞንዲያራ ጃፓን በኢትዮጵያ የሚከናወኑ የልማት ሥራዎችን በመደገፍ አጋርነቷን እያሳየች መኾኑን ገልጸዋል፡፡ ከዚህም ውስጥ የቴክኖሎጂ ዕውቀት ሽግግርን የሚያጠናክሩ ሥራዎች ዋነኞቹ መኾናቸውን ጠቁመዋል። የጃፓኑ ዓለም አቀፍ ትብብር ለሥልጠናው ስኬት አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ተናግረዋል፡፡
የሳፋሪኮም ኢትዮጵያ ተወካይ ማሳ ሚያሺታ ሳፋሪኮም ከኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ጋር በተደረገው ስምምነት መሰረት ለክህሎት ሥልጠናው በቂ የኔትወርክ አቅርቦት ተደራሽ ይደረጋል ብለዋል። ይኽ የኔትወርክ አቅርቦት ከመጀመሪያው ዙር ሥልጠናው ጀምሮ እስከሚጠናቀቅ ድረስ ቀጣይነት እንደሚኖረውም አረጋግጠዋል። ኢዜአ እንደዘገበው በመጀመሪያው ዙር ባሕር ዳር፣ ጂግጂጋ፣ ድሬዳዋ፣ ሃዋሳ፣ መቀሌ እና አዳማ ዩኒቨርሲቲዎች የክህሎት ሥልጠናው የሚጀመርባቸው መኾናቸው ታውቋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!