“መጪው ክረምት በመኾኑ ጎርፍ ያሰጋናል” የጃራ ስደተኞች መጠለያ ካምኘ ነዋሪዎች

22

ወልድያ: ግንቦት 29/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ባለፉት ጥቂት ዓመታት በኢትዮጵያ በተፈጠረው ግጭት እና አለመረጋጋት የሰው ሕይወት አልፏል፣ በርካቶች ደግሞ ከቀያቸው ተፈናቅለዋል። ይህ ዜና እስከተጠናቀረበት ጊዜ በሰሜን ወሎ ዞን ብቻ ከ 34 ሺህ 800 በላይ ተፈናቃዮች በመጠለያ ካምኘ እና ከማኀበረሰቡ ጋር ተቀላቅለው ይኖራሉ። ይህ ቁጥር በቅርቡ ከራያ አካባቢዎች የተፈናቀሉትን አይጨምርም።

የአሚኮ ጋዜጠኞች ቡድን ሃብሩ ወረዳ ጃራ ስደተኞች መጠለያ ካምኘ የሚገኙ ወገኖችን ጎብኝቷል። በካምፑ ከ11 ሺህ 200 በላይ ስደተኞች ተጠልለዋል። ይኹን እንጂ መጠለያቸው ከተሠራ የቆየ በመኾኑ በንፋስና ዝናብ የተገነጣጠለ ነው። መጪው ክረምት በመኾኑም ጎርፍ ያሰጋናል ብለዋል። ያነጋገርናቸው ተፈናቃዮች በበልግ ዝናብ በደረሰ ጉዳት ከሌሎች ጋር ተደርበው እየኖሩ ነው ብለዋል። የሰሜን ወሎ ዞን አደጋ መከላከል ምግብ ዋስትና ተጠሪ ጽሕፈት ቤት ችግሩን ቀድሞ መረዳቱን የጽሕፈት ቤቱ ኀላፊ አለሙ ይመር ነግረውናል። ጽሕፈት ቤቱ ቤቶቹን ለማደስ እና ለመጠገን ከአጋር አካላት ጋር ምክክር እያደረገ መኾኑንም ገልጸዋል።

ዘጋቢ:- ካሳሁን ኃይለሚካኤል

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየርክበ ካህናት ቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ በቤተ ክርስቲያን፣ በሀገራዊ እና በወቅታዊ ዐበይት ጉደዮች ላይ ተወያይቶ ውሳኔዎችን አሳለፈ።
Next article“የወጣቶችን የዲጂታል ሥራ ፈጠራ ክህሎት ለማስፋት የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወነ ነው” በለጠ ሞላ (ዶ.ር)