
ባሕር ዳር: ግንቦት 29/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ርክበ ካህናት የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ-ጉባኤ ተጠናቅቋል። የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ሲጠናቀቅ በዐበይት እና ወቅታዊ የሀገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ መግለጫ አውጥቷል። ቅዱስ ሲኖዶስ ያሳለፈውን ውሳኔ በሚመለከት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ መግለጫ ሰጥተዋል። ብፁዕነታቸው በመግለጫቸውም፦
✍️ በቅድስት ቤተክርስቲያን እና በሀገሪቱ መንግሥት መካከል ሊኖር ስለሚገባው መልካም የሥራ ግንኙነት በቅዱስ ፖትርያርኩ መሪነት ከመንግሥት የሥራ ኀላፊዎች ጋር የሚመካከር የብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት ልዑክ ቅዱስ ሲኖዶስ ሰይሟል።
✍️ በመላው ሀገሪቱ በተፈጠሩ ግጭቶች የሚመለከታቸው ሁሉም ባለድርሻ አካላት ከግጭት እና ከጥፋት ድርጊት ተቆጥበው የተፈጠረውን አለመግባባት እና ግጭት በውይይት እንዲሁም በምክክር እንዲፈቱ እና ዘላቂ ሰላም እንዲረጋገጥ ቅዱስ ሲኖዶስ በአጽንኦት ጥሪውን አቅርቧል።
✍️ በአዲስ አበባ ከተማ አሥተዳደር እየተከናወነ ባለው የኮሪደር ልማት ምክንያት ለፈረሱ የቤተ ክርስቲያን ይዞታዎች የከተማ አሥተዳደሩ ምትክ ቦታ በመስጠት እና ቤተክርስቲያንን ወደ መልሶ ማልማት እንድትገባ ድጋፍ በማድረግ በተሰጠው ምትክ ቦታ ላይም የከተማው ፕላን በሚፈቅደው መሠረት የመልሶ ማልማት ሥራው እንዲከናወን ቅዱስ ሲኖዶስ ወስኗል።
✍️ የሃይማኖት ጉዳዮች ረቂቅ አዋጅ ላይ ቅዱስ ሲኖዶስ በሰፊው ከተወያየ በኋላ በረቂቅ አዋጁ ሊሻሻሉ ይገባቸዋል ብሎ ያመነባቸውን የማሻሻያ ሐሳቦች በማዘጋጀት ለሚመለከተው መንግሥታዊ ተቋም እንዲላክ እና ረቂቅ አዋጁ ከመጽደቁ በፊት የተሰጡት የማሻሻያ ሃሳቦች በረቂቁ ስለመካተታቸው ክትትል የሚያደርግ ኮሚቴ ቅዱስ ሲኖዶስ ሰይሟል።
✍️ ከሀገሪቱ ውጭ ባሉ አሕጉረ ስብከት መደበኛ አገልግሎት ለመስጠት የሚላኩ አገልጋዮች በክፍሉ ሊቀጳጳስ ሲጠየቅ በሙያ ብቃታቸው፣ በምግባራቸው እና በመንፈሳዊነታቸው የተመሰከረላቸው አገልጋዮች ከሁሉም አሕጉረ ስብከት በብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት አቅራቢነት በውድድር እየተለዩ በቋሚ ሲኖዶስ ውሳኔ እንዲላኩ ቅዱስ ሲኖዶሱ ወስኗል።
✍️ የቅድስት ቤተ ክርስቲያን አሥተዳደር ዘመኑን የዋጀ እንዲኾን ቅዱስ ሲኖዶስ የ10 ዓመት መሪ ዕቅድ በማጽደቅ ወደ ትግበራ እንዲገባ የወሰነ በመኾኑ በዚሁ መሠረትም ለአፈፃፀሙ ያመች ዘንድ በባለሙያዎች ተዘጋጅቶ የቀረበውን መዋቅራዊ አደረጃጀት በማጽደቅ በሕገ ቤተክርስቲያኑ እና በቃለ ዓዋዲው ተካቶ ሥራ ላይ እንዲውል ቅዱስ ሲኖዶስ ወስኗል።
✍️ በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽሕፈት ቤት ተዘጋጅቶ የቀረበውን የ2017 ዓ.ም ዓመታዊ በጀት በማጽደቅ በሥራ ላይ እንዲውል ቅዱስ ሲኖዶስ በመወሰን ላለፉት ቀናት ሲያካሄድ የቆየውን መደበኛ ሥብሠባውን አጠናቅቋል።
ዘጋቢ፦ ቤተልሄም መኮንን
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!