“ለአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር መረጃን ሠብሥቦ ማደራጀት የሚያስችል የቴክኖሎጂ ዝግጅት ተጠናቅቋል” የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር

22

ባሕር ዳር: ግንቦት 29/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ለዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር መረጃን ሠብሥቦ ማደራጀት የሚያስችል የቴክኖሎጂ ዝግጅት መጠናቀቁን የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ገልጿል። እስካሁን ባለው ሂደትም የ3 ሺህ 900 የችግኝ ጣቢያ ማዕከላት እና የ12 ሺህ የመትከያ ስፍራዎች የጂኦ-ስፓሻል መረጃ መሠብሠቡ ተገልጿል።

የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ይሹሩን ዓለማየሁ (ዶ.ር) እንዳሉት የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ይፋ ከተደረገ ጀምሮ በመረጃ የታገዘ የቴክኖሎጂ ሥራ ሲከናወን ቆይቷል። ሀገር አቀፉ የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር እንደተጀመረም መረጃን በቀጥታ ለኅብረተሰቡ ማሳወቅ የሚያስችል ዘመናዊ ሥርዓት በማልማት ተግባራዊ መደረጉን ገልጸዋል።

ተግባራዊ የተደረገው የቴክኖሎጂ ውጤትም መረጃን በተሻለ ጥራት እና ፍጥነት ማድረስ እንዲቻል ከዓመት ዓመት እንዲሻሻል እየተደረገ እንደሚገኝም ተናግረዋል። በዚህም የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ሥራዎችን በችግኝ ተከላ ወቅት እና ከተከላ በኋላ ያሉበትን የጽድቀት እና የዕድገት ደረጃ በቴክኖሎጂ ተደግፎ የክትትል ሥራ እየተሠራ መኾኑን አስረድተዋል።

በ2016/17 ዓ.ም የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ላይም በችግኞች የጽድቀት መጠንን ክትትል ማድረግ የሚያስችል የቴክኖሎጂ ቅድመ ዝግጅት ሥራ መጠናቀቁን አስታውቀዋል። በመርሐ ግብሩ ወቅት መረጃን በጥራት እና በፍጥነት ማድረስ እንዲቻልም ሲስተሙን የማሻሻል እና መረጃን የመሠብሠብ አቅም ለማሳደግ ዝግጅት እንደተደረገ ገልጸዋል።

በስፔስ ሳይንስ እና ጂኦስፓሻል ኢንስቲትዩት የካርታ ሥራ መሪ ሥራ አስፈፃሚ ቴዎድሮስ ካሳሁን፤ የአረንጓዴ አሻራ ጂኦ-ሎኬሽን መረጃዎችን ከክልሎች የመሠብሠብ፣ የማደራጀት እና የማረጋገጥ ሥራ ይሠራል ብለዋል። በአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ መርሐ ግብር የጽድቀት ሁኔታ ምዘና ሥራዎችን በቴክኖሎጂ የታገዘ የጂኦ-ስፓሻል መረጃ ለማደራጀት እየተሠራ እንደሚገኝም ገልጸዋል።

ችግኝ የሚፈላባቸው ማዕከላት እና የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር የሚከናወንባቸውን መገኛ ስፍራዎች መረጃ የመሠብሠብ ሥራ ሢሠራ መቆየቱን ተናግረዋል። በዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር 3 ሺህ 900 የችግኝ ጣቢያ ማዕከላት እና 12 ሺህ የመትከያ ስፍራዎችን ጂኦ-ስፓሻል መረጃ መሠብሠብ እንደተቻለ አስታውቀዋል።

ኢዜአ እንደዘገበው የክልሎች ችግኝ ጣቢያ ማዕከላት እና ችግኝ መትከያ ስፍራ አብዛኛው የካርታ መረጃ የመሠብሠብ ተግባር በመጠናቀቅ ላይ መኾኑን እና በተመረጡ ቦታዎች የማረጋገጥ ሥራ እንደሚሠራም አስረድተዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየሰላም እጦቱ በሴቶች፣ ሕጻናት፣ አረጋዊያን እና አካል ጉዳተኞች ላይ ጉዳት እያስከተለ በመኾኑ ዘላቂ ሰላም ማስፈን እንደሚያስፈልግ የሴቶች፣ ሕጻናት እና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ አሳሰበ።
Next articleየርክበ ካህናት ቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ በቤተ ክርስቲያን፣ በሀገራዊ እና በወቅታዊ ዐበይት ጉደዮች ላይ ተወያይቶ ውሳኔዎችን አሳለፈ።