የሰላም እጦቱ በሴቶች፣ ሕጻናት፣ አረጋዊያን እና አካል ጉዳተኞች ላይ ጉዳት እያስከተለ በመኾኑ ዘላቂ ሰላም ማስፈን እንደሚያስፈልግ የሴቶች፣ ሕጻናት እና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ አሳሰበ።

32

ደብረ ብርሃን: ግንቦት 29/2016 ዓ.ም (አሚኮ) “ሰላምን በማጽናት በዘላቂነት እግር መትከል” በሚል መሪ መልዕክት በደብረ ብርሃን ከተማ የሚገኙ ከሁሉም ክፍለ ከተማ የተውጣጡ ሴቶች በተገኙበት ውይይት እየተካሄደ ነው። በሰላም እጦት ከሚፈተኑ የማኅበረሰብ ክፍሎች መካከል ሴቶች ቀዳሚዎቹ ናቸው።

በከተማ አሥተዳደሩ ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የአደረጃጀት ዘርፍ ኀላፊ ቅመም አሽኔ ባቀረቡት የውይይቱ መነሻ ጹሑፍ ሴቶች የሰላም ተምሳሌት በመኾናቸው ለተግባራዊነቱ ሊሠሩ ይገባል ብለዋል። የከተማው አንጻራዊ ሰላም እንዲረጋገጥ የሴቶች ሚና ከፍተኛ እንደነበር ያነሱት ኀላፊዋ የሁሉም መሠረት የኾነው ሰላም እንዲረጋገጥ የሚያስችሉ ቀጣይነት ያላቸውን ሥራዎች ሴቶች መከወን እንደሚኖርባቸው ተናግረዋል።

የደብረ ብርሃን ከተማ አሥተዳደር ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ሰሎሞን ጌታቸው ሴቶች በማኅበረሰቡ ያላቸውን ተደማጭነት በመጠቀም ዘላቂ ስላም እንዲረጋገጥ ሊሠሩ አንደሚገባ አስገንዝበዋል። ሰላሙን ተከትሎ የልማት ሥራዎች እንዲፋጠኑ እና የልማት ፍትሐዊ ተጠቃሚነት እንዲረጋገጥ መሥራት ያሻልም ብለዋል።

የአማራ ክልል ሴቶች ሕጻናት ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ምክትል ኀላፊ ንፁህ ሽፈራው የሰላም እጦቱ በተለይም በሴቶች፣ ሕጻናት፣ አረጋዊያን እና አካል ጉዳተኞች ላይ የሚያስከትለው ጉዳት የከፋ በመኾኑ ይህንን ችግር ለመፍታት የሚያስችሉ ተግባራት በዘላቂነት መከወን እንደሚገባ አሳስበዋል።
ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን በሚሠራው ሥራ ሴቶች ግንባር ቀደም መኾን ይኖርባቸዋልም ብለዋል።

የውይይቱ ተሳታፊዎችም የሰላምን አስፈላጊነት በማንሳት ሰላሙ እንዲረጋገጥ እንደሚሠሩ አረጋግጠዋል።

ዘጋቢ፦ ገንዘብ ታደሰ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበሰሜን ሸዋ ዞን የበጋ መስኖ ስንዴ በዘመናዊ መንገድ እየተሰበሰበ ነው።
Next article“ለአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር መረጃን ሠብሥቦ ማደራጀት የሚያስችል የቴክኖሎጂ ዝግጅት ተጠናቅቋል” የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር