“በጫካ የሚገኙ ወገኖችን ወደተፈጠሩበት መልካም ሥራ እንዲመለሱ ማስቻል ከሃይማኖት አባቶች እና ከሀገር ሽማግሌዎች ይጠበቃል” የደቡብ ጎንደር ዞን ዋና አሥተዳዳሪ ጥላሁን ደጀኔ

42

ባሕር ዳር: ግንቦት 29/2016 ዓ.ም (አሚኮ) “ሰላም ለሁሉም ሁሉም ለሰላም” በሚል መሪ መልእክት የወረታ ከተማ እና የፎገራ ወረዳ የሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች እና ምሁራን የሚመክሩበት ውይይት እየተካሄደ ነው። በደቡብ ጎንደር ዞን ወረታ ከተማ እና ፎገራ ወረዳ ከሃይማኖት አባቶች፣ ከታዋቂ ግለሰቦች እና ከሀገር ሽማግሌዎች ጋር የሚመክር ሕዝባዊ ውይይት እየተካሄደ ነው።

በምክክር መድረኩ ላይ የተገኙት የደቡብ ጎንደር ዞን ዋና አሥተዳዳሪ ጥላሁን ደጀኔ ተገቢ ባልኾነ ጉዞ ላይ የሚገኙትን፣ የሰው ልጅ ከተፈጠረበት ዓላማ ውጭ የኾኑትን እና በጫካ የሚኖሩትን ወገኖች ለተፈጠሩበት መልካም ሥራ ከፈጣሪ ጋር ኅብረት ወደመፍጠር ዓላማ እንዲመለሱ ማስቻል ከሃይማኖት አባቶች እና ከሀገር ሽማግሌዎች የሚጠበቅ ሥራ ነው ብለዋል።

“ሰላምን ለማስፈን እና ነፃነትን ለመጎናፀፍ ከሰዎች የምንጠብቀው ሳይኾን ከራሳችን መዳፍ የምናመርተው የመልካም ህሊና ውጤት ነው” ያሉት ዋና አሥተዳዳሪው ስለሰላም ከመስበክ፣ ስለሰላም ከመዘመር እና ነፃነትን ለመጎናፀፍ ሳንታክት መሥራት እንደሚጠበቅ ነው የገለጹት። ጦርነት አውዳሚ ነው፣ ገንዘብ ቀጣፊ ነው፣ ከምንም በላይ በገንዘብ ለማይተመነው ሰላም መሥራት እንደሚገባ አስገንዝበዋል። ሰላም ለሁሉም እንዲሰፍን ለማድረግ፣ ምርት እና ምርታማነትን ለማሳደግ መሥራት እንደሚጠበቅም ነው ያስገነዘቡት።

የመንግሥት መዋቅር በሌለበት ቀበሌ የመንግሥትን እግር የመትከል ሥራ በጽናት እና በድርብ ኀላፊነት በመውሰድ ያልተገደበ ጥረት ማድረግ እንደሚገባ ማሳሰባቸውን ከደቡብ ጎንደር ዞን የመንግሥት ኮሙኒኬሽን መምሪያ ማኅበራዊ ትስስር ገጽ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበገንዳውኃ ወንዝ ላይ የተሠራው ድልድይ ግንባታው ተጠናቅቆ ለአገልግሎት ክፍት ኾነ።
Next articleበሰሜን ሸዋ ዞን የበጋ መስኖ ስንዴ በዘመናዊ መንገድ እየተሰበሰበ ነው።