ቴሌ-ሜዲሲን

25

ባሕር ዳር: ግንቦት 29/2016 ዓ.ም (አሚኮ)ቴሌ -ሜዲሲን ማለት የጤና ጥበቃ አገልግሎቶችን ሐኪም እና ታካሚ በአካል ሳይገናኙ የቴሌኮም መሠረተ ልማቶችን በመጠቀም የሚሰጥበት መንገድ ነው፡፡ በሌላ አጠራሩ ቴሌ-ሄልዝ ወይም ኢ-ሄልዝ በመባልም ይታወቃል፡፡ የቴሌ-ሜዲሲን አገልግሎት የሚሰጠው ታካሚ ከሐኪሙ ጋር በስልክ ቀጥታ በመደዋወል አሊያም ለዚህ ዓላማ በተዘጋጀ መተግበሪያ በመታገዝ የሕክምና አገልግሎቱን የሚያገኝ ይሆናል፡፡ በሂደቱ ታካሚው የነበረውን የኋላ ታሪክ እና ምልክቶቹን በመናገር በሰጠው መረጃ መሠረት ምርመራ ከተደረገ በኋላ መድኃኒት ሊታዘዝለት ወይም ተጨማሪ ክትትል እንዲያደርግ ሊታዘዝ ይችላል፡፡

ቴሌ-ሜዲሲን ከተዘረጋ የቴሌኮም መሠረተ ልማት ጎን ለጎን በመተግበሪያም በመታገዝ በሽተኛው ከመተግበሪያው ጋር ብቻ በመገኛኘት የሕክምና ድጋፍ እና ክትትል ማግኘትም ያስችለዋል፡፡ በዓለማችን የቴሌ-ሜዲሲን አገልግሎት የሚሰጡ ብዙ ተቋማት አሉ፡፡ ሲሳሜ፣ ኤምዲላይቭ፣ ቴሌዶክ፣ አምዌል እና ሌሎችም ይህን አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛሉ፡፡

በሀገራችን ኢትዮጵያም በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ወቅት የቴሌ-ሜዲሲን አገልግሎት በተወሰነ ደረጃ ተጀምሮ እንደነበር ይታወሳል፡፡ ቴሌ-ሜዲሲን ለግንኙነት በሚጠቀማቸው መንገዶች በአራት ዓይነት መደብ ይከፈላል፡፡ አንደኛው በግንኙነት ማዕከል የሚፈጸም የቴሌ-ሜዲሲን ዓይነት ነው። የግንኙነት መሠረተ ልማት በተሟላለት ማዕከል ውስጥ በህሙማን ከሐኪሞች ጋር ቪዲዮ ኮንፍረንስን ጨምሮ በግንኙነት አማራጮች የሚገናኙበት ነው፡፡

የጤናችንን ሁኔታ በመቆጣጠር መረጃ የሚሰጡ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም የሚተገበር የቴሌ-ሜዲስን ዓይነት ደግሞ ሌላው ነው፡፡ የጤና ሁኔታችንን የተመለከተ መረጃ የሚሰጡ ማሳሪያዎች በእጅ እንደ ሰዓት የሚታሰሩ ወይም የሚለጠፉ ኾነው የሙቀት መጠንን፣ የስኳር መጠን፣ የደም ግፊትን እና መሰል የጤና ሁኔታ ጠቋሚ ምልክቶችን የሚያሳውቁ ናቸው፡፡

ከመሳሪያዎቹ የሚገኘውን መረጃ ከርቀት ኾኖ በመከታተል ድጋፍ የሚያደርግ ሐኪም ይኖራል፡፡ ሌላው የግንኙነት መሠረተ ልማትን በመጠቀም ሁለት የሕክምና መስጫ ተቋማት ስለህሙማኑ መረጃ የሚለዋወጡበት አማራጭ ያለው የቴሌ-ሜዲሲን ነው፡፡ ታካሚው ክትትል ሲያደርግበት በነበረው ተቋም ርቆ በሚሄድበት ወቅት የታካሚውን የኋላ ታሪክ፣ የምርመራ ሁኔታ እና የላብራቶሪ ውጤት ካንዱ የጤና ተቋም ወደ ሌላ ከርቀት ኾኖ ማጋራት የሚቻልበት ዓይነት ነው፡፡

አራተኛው ደግሞ ስልክን በመጠቀም ሐኪም ከታካሚ ቀጥታ ይገናኙበታል ነው፡፡ በዚህም ታካሚዎች ከርቀት ድጋፍ ለማግኘት፡፡ ቴሌ-ሄልዝ በርካታ ጥቅሞች እና የተወሰኑ እንደ ችግር የሚታዩ ውስንነቶችም አሉት፡፡ ከሚሰጣቸው ጠቀሜታዎች ውስጥ በህሙማን ወደ ሕክምና ተቋም መሄድ ሳይጠበቅባቸው ባሉበት ኾነው የጤና ጥበቃ ድጋፍ ስለሚያገኙ በጉዞ የሚጠፋን ጊዜ፣ ጉልበት እና ወጭ ይቀንሳል፡፡ ከከተማ ርቀው የሚገኙ ሰዎች አገልግሎቱን እንዲያገኙ ይረዳል፡፡ ለምሳሌ ቀዶ ጥገና ያደረጉ ታካሚዎች ባሉበት ክትትል ማድረግ የሚችሉበትን እድል ይሰጣል፡፡ ተላላፊ በሽታዎች ሲኾኑ እንዳይዛመቱ ይከላከላል፡፡

የግንኙነት ሥርዓቱ ላይ ሊደርስ የሚችል የሳይበር ጥቃት፣ የመስመር ላይ መድኃኒት ማዘዣን የሚከለክሉ ሀገራት መኖራቸው፣ የቴሌ-ሄልዝ ቴክኖሎጂዎች ሥልጠና የሚያስፈልጋቸው መኾኑ ደግሞ እንደ ውስንነት ይቆጠርበታል፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleኢትዮጵያ እና ሲንጋፖር የመግባቢያ እና የፍላጎት ስምምነት ተፈራረሙ።
Next articleበሰሜን ወሎ ዞን “ሰላምን በማጽናት በዘላቂነት እግር መትከል” በሚል መሪ ቃል ምክክር እየተደረገ ነው።