
ባሕር ዳር: ግንቦት 29/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር ታየ አጽቀሥላሴ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) እና ልዑካቸው ከሲንጋፖር ጋር እያደረጉት ያለውን ውይይት በተመለከተ ማብራሪ ሰጥተዋል፡፡ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ በማብራሪያቸው የኢትዮጵያ እና የሲንጋፖር ግንኙነት ዘመን ተሻጋሪ እና ታሪካዊ መኾኑን ገልጸዋል፡፡ የሲንጋፖር መሥራች አባት የሚባሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ሊ እ.ኤ.አ 1964 ኢትዮጵያን ጎብኝተው እንደነበር አስታውሰዋል፡፡
የሲንጋፖር አባት የሚባሉት ሊ ኢትዮጵያን በጎበኙበት ወቅት ሀገራቸው በማሊዢያ ስር ነበረች፡፡ ነጻነታቸውን ለማግኘት የአፍሪካ ሀገራትን ማግባባት ነበረባቸው፤ እ. ኤ. አ 1964 ብዙ የአፍሪካ ሀገራት ነጻ የሚወጡበት ሂደት ላይ ነበሩ፣ የጸረ ቅኝ ግዛት ትግሉ ጫፍ የወጣበት ጊዜም ስለነበር የአፍሪካ አሕጉርን መርጠዋል ይላሉ፡፡
ከሁሉም በላይ ደግሞ በቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ድጋፍ ማግኘት ነበረባቸውና ኢትዮጵያን ጎበኙ ነው የሚሉት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ፡፡ ያ ጉብኝት ለሲንጋፖራውያን ትልቅ ፋይዳ ነበረው፡፡ ሲንጋፖርን የጎበኙ ቀዳሚው አፍሪካዊው መሪም ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ናቸው፤ ዘመኑም እ. ኤ.አ 1968 ነበር፡፡
እንደ አውሮፓውያኑ የዘመን ቀመር 1965 ሲንጋፖር ነጻነቷን አገኘች፡፡ ስለዚህም ኢትዮጵያ እና ሲንጋፖር ከነጻነቷ በፊትም ከነጻነቷ በኋላም ትርጉም ያለው ግንኙነት ነበራቸው ነው የሚሉት፡፡
ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ከሰሞኑ በሲንጋፖር በነበራቸው ቆይታ በርካታ ጉዳዮችን መመልከታቸውንም ገልጸዋል፡፡ ሲንጋፖር በአንዲት ከተማ ውስጥ ያለች ሀገር ናት የሚሉት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ በፈጣን እንድገት ውስጥ ያለፈች መኾኗንም አንስተዋል፡፡ የእድገታቸው ምስጢር ትክክለኛ ፖሊሲ፣ ፖሊሲውን በሥነ ምግባር፣ ዕድገትን ማዕከል በማድረግ እና ያለ ምንም የፖለቲካ እንከን የተፈጸመ መኾኑ ነው ብለዋል፡፡ ውይይታቸው በልማት ትልቅ ለውጥ ባመጣችባቸው ጉዳዮች ዙሪያ እንደነበርም አንስተዋል፡፡
ሲንጋፖር የዓለም ዋና የፋይናንስ ማዕከል መኾኗንም ገልጸዋል፡፡ የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብርን በሚደንቅ ሁኔታ ተግባራዊ ያደረገች መኾኗንም ተናግረዋል፡፡ የአረንጓዴ አሻራ ሥራዋ የሚደነቅ መኾኑንም ገልጸዋል፡፡ የአረንጓዴ አሻራ ዝም ብሎ በቀላል ነገር የሚታይ አለመኾኑንም አመላክተዋል፡፡ ሲንጋፖራውያን ጠፍ መሬትን አረንጓዴ በማልበስ ለኑሮ ተስማሚ አድርገውታል ነው ያሉት፡፡ የሲንጋፖር የአረንጓዴ አሻራ በተምሳሌት ሊወሰድ የሚገባው ነው ብለዋል፡፡ በኢትዮጵያ ያለው የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ትክክል መኾኑን ማሳያ የሚኾነው የሲንጋፖር ሥራ ነው ብለዋል፡፡ የአረንጓዴ አሻራ የፖለቲካ ፌዝ አለመኾኑን ገልጸዋል፡፡ ለአረንጓዴ አሻራ ልዩ ትኩረት መስጠት ለትውልድ አሻራ ጥሎ ማለፍ መኾኑንም አንስተዋል፡፡
ሲንጋፖር ለዜጎቿ ያለ ምንም መተያያ እና ቅብብሎሽ ፈጣን አገልግሎት እንደምትሰጥም ገልጸዋል፡፡ በአገልግሎት አሰጣጥ ትምህርት እንደሚወሰድባቸው አንስተዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) በአረንጓዴ ልማት፣ በትምህርት፣ በፈጣን አገልግሎት፣ በከተማ ልማት ዙሪያ መምከራቸውን ገልጸዋል፡፡ የመግባቢያ ሰነዶች መዘጋጀታቸውንም ተናግረዋል፡፡ በሁለቱ ሀገራት መካከል ቀጣይነት ያለው በሁሉም ዘርፍ ምክክር እንዲቀጥል የመግባቢያ ሰነድ መፈራረማቸውንም አስታውቀዋል፡፡
በትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ዘርፍ ለመተባበር የሚያስችል ስምምነት መፈራረማቸውንም ገልጸዋል፡፡ ውጤታማ የኾነ፣ ዕውቀት የሞላበት፣ ትምህርት ያለው፣ በጎነትን የተላበሰ፣ ከኢትዮጵያ ጋር ተባብሮ ለመሥራት ፈቃደኝነት የታየበት ውይይት መኾኑን ነው የተናገሩት፡፡ በቆይታቸው በኢትዮጵያ ኢንቨስት በሚያደርጉበት ሁኔታ ላይ ከታላላቅ ተቋማት ጋር እንደሚወያዩም አንስተዋል፡፡ ውይይቱ ወንድማማችነት ያለው፤ ለመከባበር፣ ለመፈቃቀድ እና ለመደጋጋፍ መዘጋጀት ያለው ነው ብለዋል፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!