“ አንድነት ያሻግራል፣ አንድነት ያስከብራል”

109

ባሕር ዳር፡ ግንቦት 29/2016 ዓ.ም (አሚኮ) አንድ የኾኑትን የሚያከብራቸው፣ የሚያሞግሳቸው፣ እጅ የሚነሳላቸው፣ ለክብራቸው ምንጣፍ የሚያነጥፍላቸው፣ ቄጠማ የሚጎዘጉዝላቸው ብዙ ነው፡፡ አንድ የኾኑት ክፉ ዘመንን ይሻገራሉ፣ አስቸጋሪ ወቅትን ያልፋሉ፤ በድንግዝግዝ ጨለማ ብርሃን ያሳያሉ፡፡ አንድ የኾኑት ግርማን ይላበሳሉ፣ በጣለቶቻቸው ፊት ኃይልና ብርታትን ያገኛሉ፣ በሥራዎቻቸው ሁሉ ስኬትን ያስመዘግባሉ፣ በዘመቱባቸው መስኮች ሁሉ ድልን ይቀዳጃሉ፡፡

አንድነት ተከብሮ ለመኖር መሠረት ነው፡፡ መሠረቱን አንድነት ላይ ያደረገ የሚነቀንቀው፣ ነቅንቆ የሚጥለው፣ ከክብሩም የሚያሳንሰው አይኖርም፡፡ የአኩሪ ታሪኮች መሠረታቸው አንድነት ነው፡፡ አንድነት ሲኖር ጽናት ይኖራል፤ አንድነት ሲኖር አለመሸነፍ ይኖራል፤ አንድነት ሲኖር ሁልጊዜም ድል ማድረግ ብቻ ይታሰባል፡፡ አበው አንድነት ብርቱ ኃያል መኾኑን ሲያጠይቁ “ለአንድ ብርቱ ሁለት መድኃኒቱ” ይላሉ፡፡ አንድነት ያሻግራል፤ አንድነት ያስከብራል፤ አኩርቶም ያኖራልና፡፡

ግርማዊ ቀዳማዊ አጼ ኃይለ ሥላሴ ድል ለማድረግ እና በጠላት ላለመደፈር አንድነት እንደሚያስፈልግ ሲናገሩ “ አንድነት ኃይል እንደኾነ እናውቃለን፡፡ መለያየት ግን ደካማነትን እና የሰው መሣሪያነትን እንደሚያስከትል እናውቃለን፡፡ በመካከላችን ሊኖሩ የሚችሉትን ጥቃቅን ልዩነት ወደ ጎን ትተን ሁላችንም ለሚያስተባብረን ለአንድነት መድከም አለብን፡፡ እርስ በእርሳችን መነታረክ ትርፉ የሌላ ሲሳይ መኾን ነው” ማለታቸውን በሪሁን ከበደ የአጼ ኃይለ ሥላሴ ታሪክ በተሰኘው መጽሐፋቸው ጽፈዋል፡፡

መለያየት የሀገርን አንድነት የሚያፈርስ ነው፡፡ እርስ በእርስ የሚፈጠር ሁከት ለደም መፋሰስ በማድረስ ለሀገር ጉዳት ያደርሳል፤ ሀገርን ለገላጋዮች ሲሳይ ማድረግ ነው ብለው ነበር ንጉሥ ኃይለ ሥላሴ፡፡ አንድነትን ማጥበቅ ከስጋትም አደጋም ይጠብቃል፡፡ በአማራ ክልል በተፈጠረ ውስጣዊ ግጭት በአንድነት ቢሰሩ ስኬት ሊመጣባቸው የሚችሉ የፖለቲካ፣ የምጣኔ ሀብትና የማኅበራዊ ጉዳዮች ችግር ደርሶባቸዋል፡፡ በልማት ከሌሎች ጋር ተወዳዳሪ እና ቀዳሚ መኾን ሲገባው ግጭትን በማረጋገት ሥራ ተጠምዷል፡፡ ይህ ደግሞ ክልሉን በእጅጉ እየጎዳው ነው፡፡ በክልሉ ውስጥ ያለውን ግጭት እንደመነሻ ያደረጉ ከክልሉ ውጭ ያሉ አንዳንድ አካላት ክልሉን የመውረር እና ፍላጎታቸውን በኃይል የማስፈጸም እንቅስቃሴ ውስጥ ገብተዋል፡፡ ለዚህ ደግሞ ዋናው መፍትሔ አንድነትን ማጠናከር ነው፡፡ የውስጥ አንድነት ከሌለ እና እርስ በእርስ መጋደል ከበረከተ ልጠቀምባቸው የሚለው ብዙ ነውና፡፡

ከበደ ሚካኤል የዓለም ታሪክ በተሰኘው መጽሐፋቸው “የእርስ በእርስ ጦርነት ምንግዜም ቢሆን መንፈስ የሚያደነዝዝ አንጂ የሚያነቃ አይደለም” በማለት አስፍረዋል፡፡ በወልድያ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ እና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህር ማብሬ ታዴ በመሠረታዊ ጉዳዮች ላይ አንድነትን ማጠናከር ግድ ይላል፤ በመሠረታዊ ጉዳዮች ላይ የሚታዩ የአንድነት ክፍተቶችን ለመሙላት የፖለቲካ ሥራ መሥራት ይገባል ነው ያሉት፡፡ መለያየት እና ግጭት አውዳሚ ነው፣ አሁን ላይ ለተፈጠረው ግጭት መነሻው የአስተሳሰብ እና የተግባር አንድነት ስሌለ ነውም ይላሉ፡፡

የሃሳብ እና የተግባር አንድነት ባልኖረ ቁጥር ልዩነት እየሰፋ ይሄዳልም ብለዋል፡፡ ልዩነት መኖሩ ግድ ነው የሚሉት መምህሩ መሠረታዊ እና በጋራ ጉዳዮች ላይ ግን አንድነት ያስፈልጋል ነው ያሉት፡፡ ለፖለቲካው ዘላቂ መፍትሔ መስጠት ስብራቶችን ያክማል፤ ሕዝብ በስፋት የሚያነሳቸው የፖለቲካ ጥያቄዎች የሚፈቱበትን መንገድ ማሳየት እና መፍትሔዎችን ማመላከት ይገባል ነው የሚሉት፡፡ የፖለቲካ ስነ ምሕዳሩን አሳታፊ ማድረግ ፖለቲካውን ያክመዋልም ይላሉ፡፡

ግጭት ለረጅም ጊዜ የሚቆይ ጠባሳ ጥሎ ያልፋል የሚሉት መምህሩ በአማራ ክልል ያለው ግጭት ክልሉን በእጅጉ እንደሚጎደው ገልጸዋል፡፡ ውስጣዊ አንድነቱ ባለመጠበቁ እና በትክክል ባለመያዙ በክልሉ ማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊ እና ምጣኔ ሃብታዊ ኪሳራ እንዲደርስ እየኾነ ነው ብለዋል፡፡ሕዝብን አደጋ ውስጥ የሚጥሉ እርምጃዎችን መተው፣ ወደ ሰላም መምጣት፣ አንድነቱን ማምጣት ተገቢ ነው ይላሉ፡፡

ውስጣዊ ግፊቶች፣ የወረራ ሂደቶች እና የጠላትነት እንቅስቃሴዎች ባሉበት በዚህ ወቅት ውስጣዊ አንድነትን ማጣት፣ የውስጥ ለውስጥ ሽኩቻ መኖር በሕዝቡ ላይ የሚፈጥረው ተጽዕኖ ከፍተኛ ነው ብለዋል፡፡ ውስጣዊ አንድነት የሌለው ሕዝብ ጠላትን የመመለስ ኃይል አይኖረውም፣ አንድነት ኃይል ነው የሚለውን እውነታ ያጣል ነው የሚሉት፡፡ ውስጣዊ አንድነት የሌለው ሕዝብ የመጣው ሁሉ ያጠቀዋልም ብለዋል፡፡ ውጫዊ ጠላት እንዳለ እያወቁ ልዩነትን በመቻቻል አንድነት ማጠናከር ሲገባ አንድነትን ማላላት ሕዝብን ላልተገባ ጥቃት ያጋልጣል ይላሉ፡፡ ውስጣዊ አንድነትን አለማጠናከር ትልቅ የፖለቲካ ክፍተት እንደሚፈጥርም አመላክተዋል፡፡

ቀሩ ከመባል ዘግይተው መጡ መባል ይሻል የሚሉት መምህሩ አሁንም ቢሆን አንድነትን ለማምጣት ጊዜው አረፈደም፤ ለሕዝብ ጥቅም ወደ አንድነት መምጣት ይገባል ይላሉ፡፡ ልዩነቶችን በማጥበብ አንድነትን ማምጣት ካልተቻለ ሆን ከምንለው በላይ ሌላ ችግር ያመጣልም ብለዋል፡፡ እውነተኛ ውይይት፣ ሰላማዊ ምክክር በተግባር ማድረግ ይገባል ነው የሚሉት፡፡ ሰላማዊ ፍላጎቶችን እና ጥሪዎችን ወደ ተግባር መቀዬር ይገባልም ብለዋል፡፡ በሁለቱም ጎራ የሚገኙ ወገኖች ያላዩት እንዲያዩ ማድረግ፣ ለአንድ የፖለቲካ አቋም የጋራ ዓላማ እንዲኖራቸው ማድረግ እንደሚገባም አመላክተዋል፡፡

እውነትን ይዞ በድፍረት እና ብልሃት በተመላበት መንገድ መታገል፤ ሕዝብ የሚፈልጋቸውን እውነታዎች በተከታታይ በግልጽ ማሳወቅ ይገባል የሚሉት መምህሩ ሕዝብ እንዲነገረው የሚፈልጋቸውን ነገሮች ዝም ማለት ሕዝብ አመኔታ እንዲያጣ ያደርጋል ነው ያሉት፡፡ አንዳንድ ጊዜ እውነታውን ይዞ ዝም ባሉ ጊዜ ሕዝብ ተከዳን የሚል ስሜት እንዲኖረው እንደሚያደርግም ገልጸዋል፡፡ ስርዓቱን አሳታፊ ማድረግ፣ እኩልነትን ማረጋገጥ፣ የእኛ ሀሳብ ብቻ ነው ትክክል ከሚለው መውጣት ይገባልም ብለዋል፡፡

የአማራን ሕዝብ መሠረታዊ ጥያቄዎችን መፍታት፣ መስተካከል የሚገባቸውን ነገር ማስተካከል ይገባል ነው ያሉት፡፡ መፍትሔ የሚመጣው በሕዝብ መሠረታዊ ጥያቄዎች ከሁሉም ወገን የሀሳብ እና የተግባር አንድነት ሲኖር ነውም ብለዋል፡፡ ሀሳብ ማዋጣት እና ለሕዝብ ጥቅም በአንድነት መቆም በአጭር ጊዜ ለውጥ ያመጣል ነው ያሉት፡፡ በዚህ ዘመን የሚመከረውም የሚያዋጣውም ሰላማዊ የትግል አቅጣጫ መኾኑንም አመላክተዋል፡፡

ሰላማዊ ያልኾኑ የትግል አቅጣጫዎች ሕዝብን እንደሚጎዳና አውዳሚ እንደኾንም ተናግረዋል፡፡ ጦርነት እየረዘመ በሄደ ቁጥር ሕዝብ በማኀበራዊ፣ በምጣኔ ሀብታዊ እና በፖለቲካ ጉዳዮች እየተጎዳ እንደሚሄድም አንስተዋል፡፡ የክልሉ መንግሥት ሕዝብ አንገብጋቢ ጥያቄዎች ናቸው ብሎ የሚያነሳቸውን ጥያቄዎች በትኩረት መያዝ እንደሚገባውም አመላክተዋል፡፡ የወሰን እና የማንነት ጥያቄዎችን በድል ማጠናቀቅ እንዲገባም ገልጸዋል፡፡ በወሰን እና በማንነት ጉዳዮች በተመለከተ ሕዝብ፣ የፖለቲካ ሊሂቃን እንዲኹም ምሁራን አስተዋጽዖ ሊያደርጉ ይገባል ነው ያሉት፡፡ የወሰን እና የማንነት ጉዳዮችን በሰላማዊ መንገድ በሕግ አግባብ ማሸነፍ እና እልባት መስጠት ለአማራ ሕዝብ ትልቅ ትርጉም እንዳለውም ገልጸዋል፡፡ የክልሉን አንድነት ለማጽናት እና ለማጠናከር ሚናቸው የጎማ መኾኑንም አንስተዋል፡፡

ሕዝብን ወደ አንድ አቅጣጫ የሚያመጣ መሪ እና የአመራር ጥበብ እንደሚያስፈልግም አመላክተዋል፡፡ ከመሪዎች ድፈረት፣ ሕዝብን የማነቃነቅ ጥበብ፣ ጥንካሬ፣ የፖለቲካ ብስለት ይፈልጋል፣ ይጠበቃልም ብለዋል፡፡ ቹቹ አለባቸው (ዶ.ር) ዳገት ያበረተው የአማራው ፍኖት በተሰኘው መጽሐፋቸው አማራ የአማራ መሠረታዊ ጥቅሞችን ማረጋገጥ፣ አንዲት ጠንካራ ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን ማረጋጋጥ መገንባት አለበት ይላሉ፡፡ አማራ በአማራ መሠረታዊ ጥቅሞች የማይደራደር ግን ደግሞ ዲሞክራሲያዊ መርሆዎች መኾን አለበት ነው የሚሉት፡፡ በዲሞክራሲያዊ መርሆዎች መመራት አለበት ሲባል በሕግ የበላይነት እና በእኩልነት ማመን፣ የራስን ባሕል፣ ታሪክና ቋንቋ ማወቅን ፣ ማበልጸግን፣ ማልማት እና መጠመቀን የሚያካትት መኾኑን ማወቅ ያስፈልጋል፡፡

የማንነት፣ የወሰን፣ የልማት እና ሌሎች ጥያቄዎች መፍትሔው በእጃችን ነው፤ ጠንካራ የአማራ መንግሥት እና ጠንካራ የአማራ የፖለቲካ ድርጅት ከፈጠርን እነዚህ ሁለት ኃይሎች ሕግን፣ ፖለቲካን እና ታሪክን ጠቅሰው በመሟገት፣ የአማራን ሕዝብ መሠረታዊ ጥያቄዎች ማስመለስ ይችላሉ ነው የሚሉት፡፡ እንዲህ አይነት አካላትን መፍጠር ካልቻልን ደግሞ እኛ አማራዎች እንደ ባለፉት ዓመታት ሁሉ ቀጣዮቹንም ዓመታት እንደቆዘምን እንኖራለን ነው የሚሉት፡፡ ውስጣዊ አንድነትን ማጠናከር፣ ችግሮችን በውይይት መፍታት፣ ለጠላት የማይመች የውስጥ ሰላምን መፍጠር ያሻግራሉ፤ ያስከብራሉ፡፡ ትውልድንም ያኮራሉ፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበአማራ ክልል ሰሜን ጎጃም ዞንን ከማዕከላዊ እና ምዕራብ ጎንደር ዞኖች ጋር የሚያስተሳስሩት የመንገድ ፕሮጀክቶች አፈጻጸምን ለማሻሻል እየተሠራ ነው።
Next articleበደቡብ አፍሪካ የተካሄደው ምርጫ የዴሞክራሲ መርኾዎችን ያከበረ እንደነበር ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ተናገሩ።