
ባሕር ዳር: ግንቦት 29/2016 ዓ.ም (አሚኮ)በ5 ነጥብ 4 ቢሊየን ብር ወጪ የሚገነቡትን የዱር ቤቴ – ቁንዝላ – ገለጎ – መተማ ኮንትራት አንድ እና ሦስት መንገድ ፕሮጀክቶች አፈጻጸም ለማሻሻል እየተሠራ መኾኑን የኢትዮጵያ መንገዶች አሥተዳደር አስታወቀ፡፡ በአማራ ክልል ሰሜን ጎጃም ዞንን ከማዕከላዊ እና ምዕራብ ጎንደር ዞኖች ጋር የሚያስተሳስሩት የኮንትራት አንድ ዱር ቤቴ – ቁንዝላ – ሻውራ – ፍንጅት እንዲሁም የኮንትራት – ሦስት የገለጎ – ገንዳ ውኃ መንገድ ፕሮጀክቶች አፈጻጸም ለማሻሻል እየተሠራ መሆኑ ተገልጿል፡፡
የመንገድ ግንባታዎቹ በጥቅሉ 260 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትሮችን የሚሸፍኑ ሲኾን የአዲስ አበባ – ደብረ ማርቆስ – ባሕር ዳር እና የጎንደር – አዘዞ – መተማ ዋና መንገዶችን የሚያገናኙ ናቸው፡፡ አሁን ላይ የዲዛይን፣ የአፈር ቆረጣ እና ጠረጋ፣ የሰብቤዝ እንዲሁም የተፋሰስ እና የድልድይ ሥራዎች መሠራታቸውን የኢትዮጵያ መንገዶች አሥተዳደር መረጃ አመላክቷል፡፡
በተጨማሪም የአስፋልት ንጣፍ ለመጀመር የሚያስችሉ የክሬሸር እና የአስፋልት ፕላንት ተከላ መካሄዱ ተገልጿል፡፡ የመንገድ ፕሮጀክቶቹ ሲጠናቀቁ የዱር ቤቴ፣ ይስማላ፣ ሊበን፣ ቁንዝላ፣ ዱባባ፣ ሽንፋ እና ሌሎች በርካታ ከተሞችን ደረጃውን በጠበቀ መንገድ እንደሚያገናኙ ተጠቁሟል፡፡ ይህም በአካባቢው በስፋት የሚመረቱትን ጤፍ፣ ስንዴ፣ በቆሎ፣ ሽንብራ፣ ሰሊጥ፣ ጥጥ እና መሰል የአዝርዕት ምርት ውጤቶችን በቀላሉ ወደ ማዕከላዊ ገበያ ለማድረስ ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል ተብሏል፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
