
ባሕር ዳር: ግንቦት 29/2016 ዓ.ም (አሚኮ)በአማራ ክልል በዘንድሮ የክረምት ወቅት ከ8 ሚሊዮን በላይ የሕብረተሰብ ክፍሎችን በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ለማሳተፍ ዝግጅት እየተደረገ መኾኑን የክልሉ ወጣቶች እና ስፖርት ቢሮ ገለጸ። በክረምቱ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ከሚሳተፉት መካከል ከ5 ሚሊዮን በላይ የሚኾኑት ወጣቶች እንደሚኾኑ ተገልጿል።
የቢሮው ምክትል ኀላፊ ተሾመ ፈንታው በክልሉ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ላይ የሕብረተሰቡ ተሳትፎ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱን ተናግረዋል። በክረምቱ የበጎ ፈቃድ አገልግሎትም በርካታ የማኅበረሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ለማድረግ መታቀዱን አስረድተዋል። ለስኬታማነቱም የእቅድ ማስተዋወቅ፣ የተሳታፊዎች ልየታ እና ሌሎችም የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች በመከናወን ላይ እንደሚገኙ ገልጸዋል።
ተሳታፊ ወጣቶች እና ሌሎች የማኅበረሰብ ክፍሎችም በገንዘባቸው፣ በቁሳቁስ አቅርቦት፣ በጉልበታቸው እና በእውቀታቸው ከ6 ቢሊዮን ብር በላይ የሚገመት አስተዋጽኦ ያበረክታሉ ተብሎ እንደሚጠበቅም ተናግረዋል። አቶ ተሾመ እንዳመለከቱት ለሚከናወኑ ተግባራት ጥብቅ ክትትል እና ቁጥጥር በማድረግ የመንግሥትን የልማት ክፍተት በመሙላት ወደ እድገት የሚደረገውን ጉዞ ለማቀላጠፍ እንዲያግዝ በትኩረት ይሠራል።
የሚከናወኑ ተግባራትም የአቅመ ደካሞች ቤት ግንባታ እና እድሳት፣ ማዕድ ማጋራት፣ አረንጓዴ አሻራ፣ የጤና አጠባበቅ፣ የማጠናከሪያ ትምህርት እና ሰላምን ማስጠበቅን ጨምሮ በሌሎችም በተለያዩ 14 የሥራ ዘርፎች እንደሚካሄድ አብራርተዋል። የበጋ በጎ ፈቃድ ተሳታፊዎች ሲያደርጉ የቆዩትን ድጋፍ በክረምቱ ወቅትም አጠናክረው እንዲቀጥሉ መልዕክት አስተላልፈዋል።
እንደ ኢዜአ ዘገባ በአማራ ክልል በዘንድሮ የበጋ ወራት በተካሄደ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ከ1 ሚሊዮን በላይ ወጣቶችን በማሳተፍ ውጤታማ ሥራዎች መከናወናቸውም ተጠቅሷል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
