
ባሕር ዳር: ግንቦት 28/2016 ዓ.ም (አሚኮ)በሁለት ተርባይኖች ኃይል እያመነጨ የሚገኘው ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ በ2016 በጀት ዓመት 10 ወራት ከዕቅዱ የ26 በመቶ ብልጫ ያለው የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨቱን የኃይል ማመንጫዎች ኦፕሬሽን ዘርፍ ገለፀ፡፡
በዘርፉ የእቅድ ቢሮ ሥራ አስኪያጅ ወይዘሮ ጥሩወርቅ ሽፈራው እንደገለጹት ግድቡ በበጀት ዓመቱ 10 ወራት 2 ሺህ 152 ነጥብ 8 ጊጋ ዋት በሰዓት የኤሌክትሪክ ኃይል ለማመንጨት አቅዶ 2 ሺ 711 ጊጋ ዋት በሰዓት አመንጭቷል። ይኽም ከእቅዱ የ26 በመቶ ብልጫ ያለው መኾኑን ጠቁመዋል። ግድቡ የተሻለ ውኃ መያዙን እና ሁለቱ ተርባይኖች በሙሉ አቅማቸው ኃይል እንዲያመነጩ መደረጉ ለእቅድ አፈፃፀሙ ከፍ ማለት ምክንያት እንደሆነ ሥራ አስኪያጁ አስታውቀዋል።
እንደ ወይዘሮ ጥሩወርቅ ገለጻ ባለፋት 10 ወራት በአጠቃላይ ከመነጨው የ16 ሺ 900 ጊጋ ዋት በሰዓት የኤሌክትሪክ ኃይል ውስጥ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የ16 በመቶ ድርሻ አለው። ኃይል በማመንጨት ላይ የሚገኙት የግድቡ ሁለቱ ተርባይኖች እያንዳንዳቸው 375 ሜጋ ዋት የማመንጨት አቅም ያላቸው ሲኾን በግድቡ ላይ የሚተከሉት ቀሪ 11 ዩኒቶች ኃይል ማምረት ሲጀምሩ አኹን በሀገሪቱ ያለውን የማመንጨት አቅም በ83 በመቶ ያሳድገዋል ተብሎ ይጠበቃል።
እንደ ሴክሬታሪያቱ መረጃ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት ሙሉ በሙሉ ሲጠናቀቅ 5 ሽህ 150 ሜጋ ዋት የማመንጨት አቅም የሚኖረው ሲኾን ዓመታዊ የኃይል ምርቱም 15 ሺ 760 ጊጋ ዋት በሰዓት ይኾናል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
