
ሁመራ፡ ግንቦት 28/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል ወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን በቃብትያ ሁመራ ወረዳ እንደሀገር የተፈጥሮን ምህዳር ለመጠበቅ ለአረንጓዴ አሻራ መርሐግብር የሚውል የተለያዩ የችግኝ አይነቶችን ዝግጁ ማድረጋቸው ነው የተገለጸው። እየተደረገ ያለው ዝግጅትም በዞኑ ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች ጉብኝት ተካሂዷል።
በጉብኝቱም የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን አሥተዳዳሪ አሸተ ደምለው፣ የዞኑ ከፍተኛ መሪዎች እና የቃብትያ ሁመራ ወረዳ የሥራ ኀላፊዎች ተገኝተዋል። በወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን የቃብትያ ሁመራ ወረዳ አሥተዳዳሪ አታላይ ታፈረ ለችግኝ ማልሚያው ከ1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት መመደቡን ገልጸዋል። ከ20 ሰዎች በላይ የሥራ ዕድልን እንደተፈጠረላቸውም አንስተዋል።
የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብሩን እንደ ሀገር እየተሳተፍን ቆይተናል ያሉት አሥተዳዳሪው ችግኞችን ከባሕርዳር ማስመጣታቸውን ነው የገለጹት። በወረዳው ከ175 ሺህ ችግኝ በላይ ማፍላታቸው በጥሩ ተሞክሮ የሚወሰድ እንደሆነ ነው የተናገሩት። በዞኑ የአየር ንብረት ምህዳሩን ለማስተካከልም ትልቅ አስተዋፅኦ አለው ብለዋል።
“ሰላማችን እያስጠበቅን ጎንለጎን የልማት ሥራዎችን እየሠራን ነው” ሲሉም ነው ያብራሩት። የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን መምሪያ በማኅበራዊ ትስስር ገጹ እንዳለው በቀጣይም ከዚህ በተሻለ የችግኝ ጣቢያዎችን እንደሚያስፋፉ ጠቁመው በመጭው ወር ኀብረተሰቡን በማሳተፍ ችግኞቹ በተዘጋጀላቸው ቦታ እንደሚተከሉ አሳስበዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
