
ባሕር ዳር: ግንቦት 28/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጠቅላይ ጸሐፊ ሊቀ ትጉሃን ቀሲስ ታጋይ ታደለ ከአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ዲጂታል ሚዲያ ክፍል ጋር በነበራቸው ቆይታ ስለ ጉባኤው ሥራዎች፣ ስለ ኢትዮጵያ ወቅታዊ እና የወደፊት ጉዞ እንዲሁም ጉባኤው ከኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ጋር ምን ተግባራትን እያከናወነ እንደኾነ ሃሳባቸውን አካፍለዋል።
የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ሰው ሠራሽ እና የተፈጥሮ አደጋዎችን በመከላከል ሰላሞ የተረጋገጠባት ኢትዮጵያ እንድትኖር ሰፊ ጥረቶችን ሲያከናውን መቆየቱን አውስተዋል። ለአብነትም የሃይማኖት ግጭት እንዳይከሰት ውጤታማ የመከላከል ሥራዎችን አከናውኗል፣ በሰሜኑ የሀገሪቱ አካባቢም ጦርነት እንዳይከሰት ስድስት ጊዜ ያክል ጥረቶችን አድርጓል። የዓለምን ሕዝብ ተስፋ ያስቆረጠውን የኮረና ቫይረስ ወረርሽኝ ኢትዮጵያውያን በየእምነታቸው በጸሎት እንዲከላከሉት እና የሚሰጡ ሳይንሳዊ ምክረ ሃሳቦችን ተግባራዊ እንዲያደርጉ ሰፊ የቅስቀሳ ሥራዎችን ሠርቷል ብለዋል።
ሀገሪቱ ያለችበትን ወቅታዊ ችግር እንረዳለን ያሉት ቀሲስ ታጋይ ታደለ ጉባኤው ባይኖር ሀገሪቱ ከዚህ የበለጠ ቀውስ ልታስተናግድ እንደምትችል ተናግረዋል። ኢትዮጵያ በብዙ መከራ እና ስቃይ ውስጥ እያለፈችም ቢኾን ወደፊት ብሩህ ጊዜ ይመጣል የሚሉት ቀሲስ ታጋይ ታደለ ኢትዮጵያውያን ብንሰክን፣ ብንነጋገር፣ ብንደማመጥ እና ችግሮችን በምክክር ብንፈታ የተሻለች ሀገር እንገነባለን ነው ያሉት።
ኢትዮጵያውያን በሺህ ዓመታት የተገነባ አብሮነት አለን ነገር ግን በሂደት እንደ ቁርሾ የሚመስሉ ችግሮች ይስተዋላሉ። እነዚህን ችግሮች በማወራረድ ሳይኾን በፍቅር እና በይቅር ባይነት ማከም ነው የሚገባን ብለዋል። የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ከሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ጋር በቅርበት እየሠራ እንደሚገኝም የጉባኤው ጠቅላይ ጸሐፊ ሊቀ ትጉሃን ቀሲስ ታጋይ ታደለ ገልጸዋል።
የምክክር ኮሚሽኑ ካሉት አምስት ባለድርሻ አካላት አንዱ የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ እንደኾነ ያስታወሱት ቀሲስ ታጋይ ታደለ በጉባኤው በኩል ከፌዴራል እስከ ወረዳ ድረስ ተሳታፊዎችን የመለየት ሥራ እየሠራ እንደኾነ ተናግረዋል። የተለያዩ ቤተ-እምነቶች ለምክክር ኮሚሽኑ አጀንዳዎችን እያስገቡ እንደኾነም ገልጸዋል። ችግሮች ቢኖሩ እንኳ ጉባኤው ከምክክር ኮሚሽኑ ጋር በመኾን እንደሚፈታቸው ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጠቅላይ ጸሐፊ ሊቀ ትጉሃን ቀሲስ ታጋይ ታደለ “በምክክሩ በማጀት ውስጥ የሚወሩ፣ በጫካ ውስጥ የሚነገሩ እንዲኹም ትናንት እንደወንጀል የሚታዩ ጉዳዮች ወደ ጠረጴዛ መጥተው መፍትሄ ሊፈለግላቸው ይገባል” ብለዋል። በምክክሩም የተሻለው እና የብዙኃኑ ሃሳብ ገዥ ኾኖ ይወጣል፤ ይህም አስተማማኝ ሰላምን ለመገንባት ያስችላል ብለው እንደሚያምኑ ተናግረዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
