ሰላምን የማስፈን ትልቅ ኀላፊነታቸውን ለመወጣት ቁርጠኛ መኾናቸውን የሃይማኖት አባቶች ገለጹ፡፡

30

ደሴ: ግንቦት 28/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በደሴ ከተማ አሥተዳደር ከሃይማኖት አባቶች ጋር በወቅታዊ የሰላም ጉዳይ ዙሪያ ምክክር ተካሂዷል፡፡ በውይይቱ የአማራ ክልል የጸጥታ ችግሮች እና እየተከናወኑ ያሉ ሥራዎች በመነሻነት ቀርበዋል፡፡ የክልሉን ሰላም ወደነበረበት ለመመለስ የሁሉም ድርሻ ወሳኝ መኾኑ ተነስቷል።

በኢትዮጵያ ወንጌላዊት ቤተክርስተያን መካነእየሱስ ደሴ ማኀበረ ምዕመናን ቄስ እና አገልጋይ ዝናህ ሁሴን ሰላምን በማሰፈን የእምነት አባቶች ትልቅ ድርሻ እንዳላቸው እያስተማሩ እንደኾነም ጠቅሰዋል፡፡ የደሴ ከተማን ሰላም ለማስጠበቅ እና ልማቱ ተጠናክሮ እንዲቀጥል የበኩላቸውን እንደሚወጡም ነው የገለጹት፡፡

ሁሉም አካል ለሰላም ቅድሚያ በመስጠት ውይይትን የመጀመሪያ አማራጭ ማድረግ እንዳለበትም አሳስበዋል፡፡ የደሴ ከተማ ኡለማ ምክር ቤት የኢማሞች ተጠሪ ሼህ ዒሳ በሪሁን የሰው ልጆች ሁሉ ያለሰላም ዋጋ የላቸውም በማለት እርሳቸውም ይህንን አስተምህሮ እየተገበሩ እንደኾነ ተናግረዋል፡፡ በአንደበታችን የምንናገረውን ሰላም ልንኖረው ይገባል ያሉት ሼህ ኢሳ የእምነት አባቶች በትኩረት ልንሠራበት ይገባል ብለዋል፡፡

የደሴ ከተማ ቤተክህነት የሃይማኖት መምህር ሊቀ መዘምራን አክሊሉ አረጋዊ በበኩላቸው ዘመኑን የዋጀ የእምነት አስተምህሮ ለሰላም መምጣት የላቀ ትርጉም እንዳለው በመግለጽ ከማስተማር ባለፈም ሰላምን ልንኖረው ይገባል ነው ያሉት፡፡ በከተማዋ እየተተገበሩ ያሉ የልማት ሥራዎች አበረታች ናቸው ያሉት የእምነት አባቶች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ሰላምን በማስጠበቅ የበኩላቸውን እንደሚወጡ አረጋግጠዋል፡፡

የደሴ ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ሳሙኤል ሞላልኝ የከተማዋን ሰላም ለማስጠበቅ በትኩረት እየተሠራ መኾኑን ነው የገለጹት፡፡ ማኀበረሰቡን በየደረጃው በማወያየት ለሰላም ዘብ እንዲቆሙ የማድረግ ሥራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ ብለዋል፡፡ የእምነት አባቶቹ ለተሠራው ልማት ዕውቅና መስጠታቸው በቀጣይ ሰላምን በዘላቂነት በማስቀጠል ሌሎች ልማቶች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ያስችሉናል ብለዋል፡፡

የሃይማኖት ተቋማቱ የሚያነሷቸውን ጥያቄዎች ደረጃ በደረጃ እየፈታን ነው ያሉት ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ሳሙኤል ሞላልኝ ሌሎችን በቀጣይ ለመፍታት ጥረት ይደረጋል ነው ያሉት፡፡

ዘጋቢ:- ደጀን አምባቸው

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየከተማ አሥተዳደሩ ባደረገው የገንዘብ እና የክህሎት ድጋፍ የተሻለ እየሠሩ እንደኾነ በደሴ ከተማ የተደራጁ ኢንተርፕራይዞች ገለጹ።
Next article“በምክክሩ በማጀት ውስጥ የሚወሩ፣ በጫካ ውስጥ የሚነገሩ እንዲኹም ትናንት እንደወንጀል የሚታዩ ጉዳዮች ወደ ጠረጴዛ መጥተው መፍትሄ ሊፈለግላቸው ይገባል” ቀሲስ ታጋይ ታደለ