
ደሴ: ግንቦት 28/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የደሴ ከተማ አሥተዳደር ሥራ እና ሥልጠና መምሪያ የበጀት ዓመቱን የ11 ወራት የዕቅድ አፈጻጸም፣ የ60 ቀን አፈጻጸሙን እና የቀሪ 100 ቀናት የዕቅድ ትውውቅ አካሂዷል። ውይይቱን የመሩት የደሴ ከተማ አሥተዳደር ምክትል ከንቲባ ሽመልስ ጌታቸው ከተማ አሥተዳደሩ ለኢንተርፕራይዞች እና አንቀሳቃሾች ተገቢውን ድጋፍ እና ክትትል እያደረገ ነው ብለዋል።
በሕገ ወጥ መንገድ የተያዙ ሼዶች እና ኮንቴነሮች እንዲሁም ቦታ ወስደው ለሌላ ዓላማ ያዋሉ ኢንተርፕራይዞች ላይ ከተማ አስተዳደሩ ሕጋዊ መንገድን ተከትሎ እርምጃ እንደሚወሰድም አስረድተዋል። የመምሪያው የ11 ወራት ዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርት ቀርቦም ውይይት ተደርጎበታል።
በአጠቃላይ በ26 ሚሊዮን ብር ሼድ ተገንብቶ ለ10 ኢንተርፕራይዞች መተላለፉን እና ወደ ሥራ ስለመገባቱ ነው ምክትል ከንቲባው የተናገሩት።
በሰኞ ገበያ ክፍለ ከተማ በገራዶ ቀበሌ 2 ነጥብ 8 ሄክታር መሬት በመለየት ሰባት ሼዶችን ለመገንባት በከተማ አሥተዳደሩ 50 ሚሊዮን ብር ወጪ ተደርጎ በሂደት ላይ መኾኑ ነው የተገለጸው። መምሪያው ከወይዘሮ ስኂን ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ጋር በመተባበር ለኢንተርፕራይዞች የኢንደስትሪ ኤክስቴንሽን ድጋፍ አድርጎላቸዋል።
አሚኮ ያነጋገራቸው በከተማ አሥተዳደሩ ድጋፍ ተደርጎላቸው ወደ ሥራ የገቡ ኢንተርፕራይዞች እንደተናገሩት የከተማ አሥተዳደሩ ባደረገው የገንዘብ እና የክህሎት ድጋፍ የተሻለ እየሠሩ እንደኾነ አስረድተዋል። የደሴ ከተማ አሥተዳደር ሥራ እና ሥልጠና መምሪያ ኅላፊ ነፃነት ቢሰጥ ሥራ ፈላጊ ወጣቶችን በአግባቡ እና በሕጉ መሠረት በመመልመል፣ በማደራጀት እንዲሁም ተከታታይ ሙያዊ ድጋፍ በመስጠት ወደ ሥራ እንዲገቡ ተደርጓል ብለዋል።
ዘጋቢ :-አንተነህ ፀጋዬ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
