
ባሕር ዳር: ግንቦት 28/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የኢትዮጵያ እና የሳዑዲ አረቢያን የኢንቨስትመንት እና የንግድ አጋርነት ለማጠናከር እየተሠራ መኾኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል። በሳዑዲ አረቢያ የንግድ ምክር ቤት ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት የተመራ 79 አባላትን የያዘ የሳዑዲ አረቢያ የኢንቨስትመንት እና የንግድ ልዑካን ቡድን ትላንት ማምሻውን አዲስ አበባ ገብቷል።
ልዑካን ቡድኑ ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርስ የፕላን እና ልማት ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ (ዶ.ር)፣ የቱሪዝም ሚኒስትር አምባሳደር ናሲሴ ጫሊ እንዲሁም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምሥጋኑ አርጋ ተቀብለዋቸዋል። ልዑካን ቡድኑ በኢትዮጵያ በሚኖረው የሦስት ቀናት ቆይታ የማምረቻ ቦታዎችን የሚጎበኝ ሲኾን፤ በኢትዮጵያ ያሉ የኢንቨስትመንት እና የንግድ አማራጮችን በተመለከተ ገለጻ ይደረግለታል ተብሏል።
ልዑካን ቡድኑ በኢትዮጵያ የሚያደርገው ጉብኝት የሀገራቱን ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ እንደሚያሸጋግረውም ተጠቁሟል። የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምሥጋኑ አርጋ ኢትዮጵያ እና ሳዑዲ አረቢያ በተለያዩ ዘርፎች ለረዥም ጊዜ የቆየ ጠንካራ አጋርነት አላቸው ብለዋል።
ይህን አጋርነት በተለይም በንግድ እና ኢንቨስትመንት ለማስፋት ትኩረት መደረጉን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ በምታከናውናቸው ተግባራት ተመራጭ የኢንቨስትመንት መዳረሻ እንድትኾን አስችሏታል ብለዋል። በተለይም ባለፉት የለውጥ ዓመታት በመስኩ የተከናወኑ ሥራዎች በሀገሪቱ የኢንቨስትመንት ሥራ መሳካት ምቹ መደላድል መፍጠሩን ነው ያስረዱት።
ይህንንም ተከትሎ የሳዑዲ አረቢያ ባለሃብቶች በኢትዮጵያ ያለውን ምቹ የኢንቨስትመንት አማራጮችን ተጠቅመው ኢንቨስት እንዲያደርጉም ጥሪ አቅርበዋል። የሳዑዲ ባለሃብቶች በኢትዮጵያ በተለያዩ ኢንቨስትመንት ዘርፎች ተሰማርተው ውጤታማ እንዲኾኑ መንግሥት አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግም አረጋግጠዋል።
የሳዑዲ አረቢያ የንግድ ምክር ቤት ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ሐሰን ሙጂብ ሀገራቸው ከኢትዮጵያ ጋር ባላት ጠንካራ ግንኙነት የተሰማቸውን ደስታ ገልጸዋል። የሳዑዲ ባለሃብቶች በኢትዮጵያ በተለያዩ የኢንቨስትመንት መስኮች ለረዥም ጊዜ ተሰማርተው መቆየታቸውን አስታውሰው ግንኙነቱ የበለጠ እንዲጠናከር እንፈልጋለን ነው ያሉት።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
