
ባሕር ዳር: ግንቦት 28/2016 ዓ.ም (አሚኮ)ሀገራዊ ምክክሩ ለሀገረ መንግሥት ግንባታ ትልቅ ግብዓት የሚገኝበት መኾኑን ተሳታፊዎች ተናግረዋል። በአዲስ አበባ የአጀንዳ ማሠባሠብ ምዕራፍ በተፅእኖ ፈጣሪ ግለሰቦች ተሳታፊ የኾኑት አቶ መርጊያ በቀለ እንደገለጹት ሀገራዊ ምክክሩ ኢትዮጵያን እንዴት እናስቀጥላት የሚለውን አመላካች ነገር ይዞ የሚመጣ በመኾኑ ለሀገረ መንግሥት ግንባታ ትልቅ ግብዓት ነው።
ምክክሩ የጋራ ሀገራዊ አጀንዳ እንዲኖረን ቅድመ ሁኔታ ነው የሚሉት አቶ መርጊያ ሀገርን ወደ ሚመጥን እና አንድነትን ወደሚያጎላ ብሔራዊ አጀንዳ ይወስዳታል ብለዋል። ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉትን ችግሮች ለመፍታት በግለሰብ እና በቡድን ደረጃ የሞከሩ ቢኖሩም ስኬታማ እንዳልነበሩ አስታውሰው ችግሩን መፈታት የሚችለው ሕዝብ ሲወያይ እና በውስጡ ያለውን ሃሳብ አውጥቶ ሲናገር መኾኑን ተናግረዋል።
እንደ አቶ መርጊያ ገለጻ ኢትዮጵያ ወደፊት እንዳትሻገር እንቅፋት የኾኑባትን ችግሮች ሕዝብ ያለ ልዩነት ተሠባሥቦ እንዲመክርባቸው መደረጉ ትልቅ ዕድል ነው። በግለሰብ፣ በማኅበረሰብ እና በመንግሥት ደረጃ ያሉ ችግሮችን ለመለየት እና መፍትሔ ለማበጀት ውይይት እየተደረገ መኾኑ እንዳስደሰታቸው ተናግረው ምክክሩ ዘላቂ ሰላሟ የተረጋገጠ ኢትዮጵያን ለትውልድ ለማስተላለፍ ትልቅ እርምጃ ነው ብለዋል።
በምክክሩ መንግሥት የመጀመሪያው ባለድርሻ ነው የሚሉት አቶ መርጊያ በውይይቱ ወቅት የሚቀርቡ ሃሳቦች ሀገርን የሚያጸኑ እስከኾኑ ድረስ ተቀብሎ ተግባራዊ ሊያደርጋቸው እንደሚገባ ጠቁመዋል። በሂደቱ ኮሚሽኑ ያለ ማንም ጣልቃ ገብነት በነጻነት የምንወያይበት ዕድል አመቻችቷል የሚሉት አቶ መርጊያ በምክክሩ የሚሳተፉ ተሳታፊዎች የምንፈልጋት ኢትዮጵያን ለማግኘት እርስ በእርስ በመደማመጥ መወያየት አለብን ነው ያሉት።
በምክክሩ የአዲስ አበባ አካል ጉዳተኞችን በመወከል ተሳታፊ የኾኑት ፓስተር እስክንድር ሻወል በበኩላቸው ኢትዮጵያ ውስጥ እርስ በእርስ ባለመግባባት በሚፈጠሩ ግጭቶች የወጣቶች ሕይወት መቅጠፉን አስታውሰው ሀገራዊ ምክክሩ በግጭት የተናጋውን አንድነት እንደሚያጠናክር አመልክተዋል። እስከ አሁን ድረስ ኢትዮጵያ ውስጥ ዜጎች የሃሳብ ልዩነቶቻቸውን ቁጭ ብለው ተነጋግረው ከመፍታት ይልቅ የመገዳደል ፖለቲካ ሲያራምዱ ነበር ያሉት ፓስተር እስክንድር ምክክሩ አለመግባባቶችን በውይይት ለመፍታት መልካም አጋጣሚ ይዞ መምጣቱን ገልጸዋል።
ሌላኛው በተፅዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦች ቡድን ተሳታፊ የኾኑት አቶ ሙስጠፋ ሺፋ እንደሚሉት ደግሞ ኢትዮጵያ በርካታ ብሔር ብሔረሰቦችን ያቀፈች ሀገር በመኾኗ እንዲሁም በኃይልም የሚፋለሙ ኃይሎች ያሉባት ሀገር በመኾኗ ምክክሩ መደረጉ ለሀገር ሰላም ትልቅ ሚና አለው። ኢፕድ እንደዘገበው ተሳታፊዎቹ በልዩነት ውስጥ አንድነትን አስጠብቆ ለመሄድም ምክክሩ ወሳኝ መኾኑን ተናግረው ምሁራን፣ ተፅዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦች እንዲሁም ሁሉም ባለድርሻ አካላት በምክክሩ ኀላፊነታቸውን ሊወጡ እንደሚገባ ጠቁመዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
