
ባሕር ዳር: ግንቦት 28/2016 ዓ.ም (አሚኮ)በማዕከላዊ ጎንደር ዞን በታች አርማጭሆ ወረዳ መንግሥት ያቀረበውን የሰላም ጥሪ የተቀበሉ 22 ታጣቂ ኃይሎች ማኅበረሰቡን ተቀላቅለዋል። የመንግሥት የሰላም ጥሪን የተቀበሉት ታጣቂዎቹ ለሰላም ዝግጁ መኾናቸውን ተናግረዋል። ለተደረገላቸው የሰላም ጥሪ መንግሥትን አመሥግነው በቀጣይ ከመንግሥት ጎን ተሰልፈው መደበኛ ሥራቸውን እንደሚጀምሩም ነው የገለጹት።
ሌሎች አካላትም መንግሥት ያመቻቸውን የሰላም ጥሪ ተቀብለው እንዲገቡ ጥሪ አቅርበዋል። የታች አርማጭሆ ወረዳ ዋና አሥተዳዳሪ አስማረ የኋላሸት በወረዳው ዘላቂ ሰላምን ለማምጣት ከሀገር መከላከያ ሠራዊት፣ ከሃይማኖት አባቶች፣ ከሀገር ሽማግሌዎች እና ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በጋራ እየተሠራ እንደሚገኝ አንስተዋል።
የታጠቁ ኃይሎች የመንግሥትን የሰላም ጥሪ ተቀብለው እንደገቡ ገልጸው የሚፈጠሩ ችግሮችን በሰለጠነ መንገድ በውይይት መፍታት ተገቢ መኾኑንም ጠቁመዋል። በሌላ በኩልም የሀገር ሽማግሌዎች እና የሃይማኖት አባቶች ለዘላቂ ሰላም እየሠሩት ያለው ሥራ አበረታች መኾኑ ተገልጿል። ከማዕከላዊ ጎንደር ዞን ኮሙዩኒኬሽን መምሪያ የማኅበራዊ ትስስር ገጽ እንደ ተገኘው መረጃ የሰላም ጥሪውን ተቀብለው ለተቀላቀሉት አካላትም ከአቀባበል ጀምሮ አስፈላጊው ድጋፍ እንደሚደረግላቸው ዋና አሥተዳዳሪው አብራርተዋል።
የ78ኛ ክፍለ ጦር ዋና አዛዥ ኮሎኔል ግርማ መሀመድ ለሰላም ዘብ መቆም፣ መረዳዳት እና መደጋገፍ እንዲሁም ለሰላም መዘመር ያለበት የሀገር መከላከያ ሠራዊት ብቻ አለመኾኑን በመገንዘብ ሁሉም ሰላም ወዳድ የኅብረተሰብ ክፍል ሰላምን ለማስፈን የበኩሉን ሁሉ እንዲወጣ አሳስበዋል፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
