በብሔረሰብ አሥተዳደሩ ያለውን ሰላም ለማጽናት ከአጎራባች ዞኖች ጋር መሥራት እንደሚገባ የኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር ነዋሪዎች ገለጹ።

21

ባሕር ዳር: ግንቦት 28/2016 ዓ.ም (አሚኮ)በኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር በሁሉም ወረዳወች እና ከተማ አሥተዳደር የሕዝብ ተወካዮች በየደረጃው ካሉ የምክር ቤት አባላት እና ከተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ጋር ምክክር ተካሂዷል። “ሀገራዊ ማንነት እና ሀገራዊ እሴት፣ የሕዝብ ተመራጮች ለሰላም ግንባታ ያላቸው ሚና” በሚል ርዕሰ ጉዳይ በተዘጋጀ ሰነድ ላይ በየአካባቢው ባሉ የመንግሥት የሥራ ኀላፊዎች እና ባለድርሻ አካላት አወያይነት ነው ምክክሩ እየተካሄደ የሚገኘው።

መንግሥት የጀመረውን የልማት እና የመልካም አሥተዳደር ተግባራት እንዲሁም የተጀመረውን ሀገራዊ የለውጥ ጉዞ አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት በምክክሩ ተነስቷል። የብሔረሰብ አሥተዳደሩ ሕዝብ ከውስጥም ከውጭም ካሉ ሕዝቦች ጋር ተባብሮ እና ተከባብሮ መሥራት እንዳለበትም ተነስቷል።
በአንድነት እና በኅብረት ውስጥ መኾን ያለውን ፀጋ መጠቀም እና ሰላሙን መጠበቅ እንደሚገባም ነው የተገለጸው።

አሁን ላይ በብሔረሰብ አሥተዳደሩ ወረዳዎች አንጻራዊ ሰላም ቢኖርም ቀጣይነት ያለው ሰላም እንዲሰፍን የውስጥ ሰላምን ለማረጋገጥ ከአጎራባች ወንድም ሕዝቦች ጋር መሥራት እንደሚገባም በአጽንኦት ተገልጿል። የብሔረሰብ አሥተዳደሩ ሕዝብ የቆየውን የመተሳሰብ እና የመተባበር ባሕልን የሚሸረሽሩ መጤ ግጭት ቀስቃሽ አስተሳሰብን ታግሎ ከማረም አንጻር ሁሉም ባለድርሻ አካላት የሚጠበቅበትን መወጣት አለበት ነው የተባለው።

አብሮነት እንዲሸረሸር የሚያደርጉ ኃይሎችን በጋራ በመመከት ዘላቂ ሰላም ለማምጣት ማኅበረሰቡ የሚጠበቅበትን ኃላፊነት በመወጣት ለጠንካራ ሀገረ መንግሥት ምስረታ የድርሻውን እንደሚወጣ በውይይቱ መግባባት ላይ ተደርሷል። የብሔረሰብ አሥተዳደሩ ምክር ቤት አፋ ጉባኤ ሀሊማ ይማም “የነገዋን ለሁላችንም የምትኾን ሀገር ለመገንባት ሁሉም የሚጠበቅበትን ኀላፊነት ሊወጣ ይገባል” ነው ያሉት። ለዚህም ውይይት አስፈላጊ መኾኑን ነው የገለጹት።

የአማራ ክልል የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ በማኅበራዊ ትስስር ገጹ እንዳለው ለውይይቱ ስኬትም በየደረጃው ያሉ የሕዝብ ተመራጮች፣ የሃይማኖት አባቶቾ፣ ሁሉም የሕዝብ አደረጃጀቶች እና በየደረጃው ያሉ መሪዎች ጉልህ ሚና ስላላቸው የሚጠበቅባቸውን ኀላፊነት እንዲወጡ አሳስበዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበአዲስ አበባ ከተማ በተካሄደው የምክክር ምዕራፍ የተሰበሰቡ አጀንዳዎች መዳረሻቸው የት ነው?
Next articleታጥቀው በጫካ ሲንቀሳቀሱ የቆዩ ኃይሎች ማኅበረሰቡን ተቀላቀሉ።