
በአማራ ክልል ምክር ቤት ዋና አፈጉባኤ ወይዘሮ ወርቅሰሙ ማሞ የተመራ የምክር ቤቱ ልዑክ በክልሉ የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመከላከል እየተሰሩ ያሉ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎችን ዛሬ በባሕር ዳር ተመልክቷል፡፡
በመስክ ምልከታው የአማራ ክልል ምክር ቤት የተለያዩ ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢዎች ተሳትፈዋል፡፡ በባሕር ዳር ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ መዳረሻቸውን ለሚያደርጉ መንገደኞች እየተደረገ ያለውን የሙቀት ልየታ ሥራና ድንገት በሽታው ቢከሰት ህክምና ለመስጠት እየተዘጋጀ የሚገኘውን በባሕርዳር የመከላከያ ሆስፒታል ቅድመ ዝግጅት ስራዎችን ተመልክተውም አስተያየት ሰጥተዋል፡፡
በክልል አቀፍ ደረጃ ቫይረሱን ለመከላከል ከተቋቋመው ግብረ ሃይል ጋርም ውይይት አድርገዋል፡፡ በውይይቱም ግብረ ሃይሉ የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል እየተሰሩ ያሉ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎችና የግንዛቤ ፈጠራ ተግባራት አፈፃጸም ቀርበዋል፡፡ ማኅበረሰቡ ስለ በሽታው መተላለፊያ መንገዶችና የመከላከያ ዘዴዎች ግንዛቤ እንዲኖረው በሁሉም አካባቢዎች አደረጃጀቶች መፈጠራቸው፣ በሁሉም ዞኖች አንድ፣ አንድ የማቆያ ቦታዎች መዘጋጀታቸው፣ ለዚህ ሥራ ብቻ አገልግሎት የሚሰጡ አምቡላንሶች መዘጋጀታቸውና ከአሁን በፊት የነበሩ ውስን ልየታ ቦታዎች ቁጥራቸው እንዲያድግ መደረጉ በጥንካሬ የተነሱ ናቸው፡፡
በሽታው ድንገት ቢከሰት ለህሙማኑ የህክምና አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችሉ የህክምና ቦታዎች መዘጋጀታቸውም በውይይቱ ተነስቷል፡፡
በሌላ በኩል የሙቀት መለያ እና የመመርመሪያ ኪት እጥረት መከሰቱና ይህም እንዲሟላ ግብረ ሀይሉ ጠይቋል፡፡ በተለይ የመመርመሪያ ኪት አለመኖሩ ውጤቱ ከአዲስ አበባ ተልኮ እስኪመጣ እየተጠበቃ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡ እየተሠሩ ካሉ ሥራዎች በተጨማሪ በክልሉ የጎብኝዎች መዳረሻ ቦታዎች ላይ ጥብቅ ቁጥጥር መደረግ እንዳለበትና አሁንም የሚደረጉ ሕዝባዊ ስብሰባዎች መቆም እንዳለባቸው ከምክር ቤቱ የተለያዩ ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢዎች ተናግረዋል፡፡
የአማራ ክልል ምክር ቤት ዋና አፈጉባኤ ወይዘሮ ወርቅሰሙ ማሞ በሽታውን ለመከላከል እየተሰሩ ያሉ ሥራዎች በጥሩ ሁኔታ እየተከናወኑ እንዳሉ መታዘባቸውን ተናግረዋል፡፡ በክልሉ በጀት መሸፈን የሚችሉ የሚያስፈልጉ ግብአቶች ከወዲሁ እንዲሟሉም ጠቁመዋል፡፡ በቂ የሆነ የሙቀት መለያና የመመርመሪያ ኪት እንዲቀርብ የፌደራል መንግሥት የተለመደ ትብብሩን ማድረግ እንዳለበትም ጠይቀዋል፡፡
ማኅበረሰቡ በበሽታው ከመያዙ በፊት የግልና የአካባቢ ንፅህናውን እንዲጠብቅም መልክት አሥተላልፈዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ኃይሉ ማሞ