“ምክር ቤቶች በሕዝብ የሚነሱ ጥያቄዎች እንዲመለሱ በትኩረት መሥራት ይጠበቅባቸዋል” አፈ ጉባዔ ታገሰ ጫፎ

25

ባሕር ዳር: ግንቦት 28/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የዴሞክራሲ ተቋማት ነጻ እና ገለልተኛ ኾነው ሀገራዊ ኅላፊነታቸውን ሊወጡ እንደሚገባ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባዔ ታገሰ ጫፎ አስታወቁ። ”የዴሞክራሲ ተቋማት ሚና በሀገረ መንግሥት ግንባታ” በሚል ርዕስ ለፌዴራል እና ለክልል ምክር ቤት መሪዎች እና ለዴሞክራሲ ተቋማት ኀላፊዎች በቢሸፍቱ ከተማ የአቅም ግንባታ ሥልጠና እየተሰጠ ነው።

በሥልጠናው ላይ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባዔ ታገሰ ጫፎ እንዳሉት ምክር ቤቶች የሕዝብ ተሳትፎን በማረጋገጥ፣ ውጤታማ የሕግ ማዕቀፍ በማዘጋጀት፣ በክትትል እና ቁጥጥር ሥራዎች በሕዝብ የሚነሱ ጥያቄዎች እንዲመለሱ በትኩረት መሥራት ይጠበቅባቸዋል።

የዴሞክራሲ ተቋማት ለሀገረ መንግሥት ግንባታ የሚያደርጉት አስተዋጽኦ ከፍተኛ መኾኑን የገለጹት አፈ ጉባኤው፤ ተቋማቱ ነጻ እና ገለልተኛ በመኾን ኀላፊነታቸውን በላቀ ደረጃ መፈጸም ይገባቸዋልም ብለዋል። በተለይ የሚዲያ ተቋማት ትክክለኛ መረጃ በማቅረብ፣ ኅብረተሰቡ ውስጥ የሚነሱ ሃሳቦችን ትኩረት ሰጥቶ በመሥራት እንደ ሀገር የጋራ የኾኑ ጉዳዮች ላይ በማተኮር የዴሞክራሲ ባሕልን ለመገንባት ሊተጉ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

ሥልጠናው የዴሞክራሲ ተቋማት በሀገረ መንግሥት ግንባታ የነበራቸውን ሚና በመዳሰስ ተጨማሪ ግብዓት በመውሰድ ተናቦ እና ተግባብቶ ለመሥራት ትልቅ እገዛ ያደርጋል ነው ያሉት አፈ ጉባዔው። በሥልጠናው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባዔ፣ ምክትል አፈ ጉባዔ፣ የመንግሥት ዋና ተጠሪ ሚንስትር እና ሚንስትር ዴኤታዎች እንዲሁም ሌሎች አካላት መገኘታቸውን ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተገኘው መረጃ ያመላክታል።

“የዴሞክራሲ ተቋማት ሚና በሀገረ መንግሥት ግንባታ” በሚል የተዘጋጀው ሥልጠና በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና በጀርመኑ ኮንራድ አዴኑር እስቲፍተንግ ቲንክ ታንክ ፖሊሲ ኢንስቲቲዩት በጋራ የተዘጋጀ ነው።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበክልሉ ዘላቂ ሰላም ለማስፈን የኅብረተሰቡን አንገብጋቢ ችግሮች በጥናት ለይቶ መፍታት የመንግሥት ቀዳሚ አጀንዳ ሊኾን እንደሚገባ የመንግሥት ሠራተኞች ገለጹ።
Next articleበኢትዮጵያ የንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት እና በሳዑዲ አረቢያ አቻው መካከል የመግባቢያ ሥምምነት ተፈረመ።