በክልሉ ዘላቂ ሰላም ለማስፈን የኅብረተሰቡን አንገብጋቢ ችግሮች በጥናት ለይቶ መፍታት የመንግሥት ቀዳሚ አጀንዳ ሊኾን እንደሚገባ የመንግሥት ሠራተኞች ገለጹ።

55

እንጅባራ: ግንቦት 28/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር የመንግሥት ሠራተኞች በወቅታዊ የሰላም፣ የልማት እና የመልካም አሥተዳደር ጉዳዮች ላይ በእንጅባራ ከተማ ምክክር አካሂደዋል። የመንግሥት ሠራተኞቹን ያወያዩት በብልጽግና ፓርቲ የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ አለሙ ሰውነት መድረኩ በብሔረሰብ አሥተዳደሩ ባለፉት ወራት የተከናወኑ ዋና ዋና ተግባራትን ለመንግሥት ሠራተኛው ለማስገንዘብ እና በቀጣይ 100 ቀናት የሚከናወኑ ዐበይት ተግባራት ላይ የጋራ መግባባት ለመፍጠር ያለመ መኾኑን ተናግረዋል።

ለመንግሥት ፖሊሲዎች እና አሠራሮች ተፈጻሚነት እና ለዘላቂ ሰላም መስፈን የመንግሥት ሠራተኛው ሚና የጎላ ነው ብለዋል። ኀላፊው የመንግሥት ሠራተኞች መንግሥት እና ሕዝብ የሰጣቸውን አደራ በአግባቡ ሊወጡ እንደሚገባም አስገንዝበዋል።

በመድረኩ የውይይት መነሻ ጹሑፍ ያቀረቡት የብሔረሰብ አሥተዳደሩ ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የፖለቲካ ዘርፍ ኀላፊ ዘለቀ ከፋለ ለሰላም እጦት መባባስ ምክንያት የኾኑ በመንግሥት መስሪያ ቤቶች አገልግሎት አሰጣጥን ማሻሻል፣ የወጣቶች የሥራ ዕድል ፈጠራ እና የዋጋ ንረቱን ማረጋጋት በቀጣይ የክረምት ወራት የሚከናወኑ ቁልፍ ተግባራት መኾናቸውንም ገልጸዋል። የውይይቱ ተሳታፊዎችም በክልሉ ዘላቂ ሰላም ለማስፈን የኅብረተሰቡን አንገብጋቢ ችግሮች በጥናት ለይቶ መፍታት የመንግሥት ቀዳሚ አጀንዳ ሊኾን እንደሚገባ አንስተዋል።

ዘጋቢ፦ ሳሙኤል አማረ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየኢትዮጵያ እና ሳዑዲ አረቢያ የንግድ እና ኢንቨስትመንት ግንኙነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ እንደሚገኝ ተገለጸ።
Next article“ምክር ቤቶች በሕዝብ የሚነሱ ጥያቄዎች እንዲመለሱ በትኩረት መሥራት ይጠበቅባቸዋል” አፈ ጉባዔ ታገሰ ጫፎ