
ባሕር ዳር: ግንቦት 28/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የኢትዮ-ሳዑዲ የንግድ እና ኢንቨስትመንት ፎረም በሳይንስ ሙዚየም መካሄድ ጀምሯል። በፎረሙ በሳዑዲ አረቢያ የንግድ ምክር ቤት ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት የተመራ 79 አባላት ያለው ልዑክ እና ባለድርሻ አካላት እየተሳተፉ ይገኛሉ።
በፎረሙ መክፈቻ ላይ ንግግር ያደረጉት የፕላን እና ልማት ሚኒስትር ፍፁም አሰፋ (ዶ.ር) የሁለቱ ሀገራት የንግድ እና ኢንቨስትመንት ግንኙነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ እንደሚገኝ ገልጸዋል። ሚኒስትሯ አክለውም ኢትዮጵያ የካፒታል ማርኬት መጀመርን ጨምሮ በተለያዩ ዘርፎች ሪፎርም በማድረግ ለኢንቨስተሮች ምቹ ሁኔታ ፈጥራለች ነው ያሉት።
የሳዑዲ አረቢያ የንግድ ምክር ቤት ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ሁሴን ሙጂብ (ዶ.ር) በበኩላቸው የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት ከፈረንጆቹ 1948 ጀምሮ የተጀመረ መኾኑን ገልጸዋል። አሁን ላይ ያለው የንግድ ግንኙነት ይኽን የረጅም ጊዜ ግንኙነት የሚገልጽ ባለመኾኑ የንግድ ግንኙነታችንን ልናጠናክር ይገባል ብለዋል። እንደ ኢቢሲ ዘገባ የፎረሙ ተሳታፊዎች የኢትዮጵያውያን አምራቾች ምርቶችን በሳይንስ ሙዚየም ተዟዙረውም ጎብኝተዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
