ሥራ ፈጣሪ ትውልድን ማፍራት ላይ ያለመ ውድድር በኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር አዘጋጅነት እየተካሄደ ነው፡፡

19

ባሕር ዳር፡ ግንቦት 28/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በሮበርት ዘእርዝ የሃካቶን ውድድር አሸናፊው ቡድን የዋንጫ እና የ10 ሺህ ዶላር ተሸላሚ ይኾናል፡፡ በኢትዮጵያውያን መካከል በሚካሄደው በዚህ ዓለም አቀፍ ሮበርት ዘእርዝ የሃካቶን ውድድር አሸናፊው ቡድን በአሜሪካ በሚካሄደው የሃካቶን ውድድር ኢትዮጵያን በመወከል የሚሳተፍ ሲኾን በዚህ ውድድር የዋንጫ እና የ10 ሺህ ዶላር ተሸላሚ ይኾናል፡፡

የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ከኢትዮጵያ የተባበሩት መንግሥታት የምግብ እና እርሻ ድርጅት (ፋኦ) ጋር በመተባበር የሮበርት ዘእርዝ የሃካቶን ውድድር ከተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢ በተውጣጡ የሀካቶን ተወዳዳሪዎች መካከል በአዲስ አበባ አይሲቲ ፓርክ ኢኖቪስኪ ኢትዮጵያ ኢንኩቤሽን ሴንተር ነው የሚካሄደው፡፡

በውድድሩ 11 ቡድኖች የተሳተፉ ሲሆን በ36 ሰዓት ውስጥ ለተሰጣቸው ተግዳሮት በሶፍት ዌር አማካይነት ለተፈጠረው ችግር በአጭር ጊዜ ውስጥ መፍትሔ በማስቀመጥ አንደኛ የወጣው ቡድን በአሜሪካ ኒዮርክ ከተማ ለሚካሄደው ውድድር ሀገሪቱን የሚወክል ይኾናል። በፕሮግራሙ ላይ የተገኙት የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ባይሳ በዳዳ (ዶ.ር) በስታርታፕ ሥነምህዳር ግንባታ ላይ እየተሠራ ያለውን ሥራ በማጠናከር ሥራ ፈላጊ ሳይኾን ሥራ ፈጣሪ ትውልድን ማፍራት ላይ እንደሚሠራ ተናግረዋል ለችግሮቻችን መፍትሔ በመስጠት ሀገርን መለወጥ እንደሚቻል የሀካቶን ውድድር አንዱ ማሳያ መኾኑን አንስተዋል፡፡

የሃካቶን ማራቶን ውድድሩ ተከፍቷል ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው ኢትዮጵያውያን ከተባበርን የጀመርነውን ለውጥ በማፍጠን በአጭር ጊዜ የምንፈልገውን የኢኮኖሚ እድገት ምዕራፍ ላይ ለመድረስ የሚያግደን ነገር አይኖርም ብለዋል፡፡ ለአየር ንብረት ለውጥ እና ለዘላቂ ግብርና ተግዳሮቶች በዲጂታል ቴክኖሎጂዎች እና በተለይም ለኢትዮጵያ ወጣቶች የፈጠራ ባለሞያዎች በዓለም አቀፍ ደረጃ የፈጠራ መፍትሄዎቻቸውን እንዲያቀርቡ እድል የሰጠ ውድድር ነው ።

የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር በማኀበራዊ ትስስር ገጹ እንዳለው ውድድሩ ለአካባቢው ማኅበረሰብ ችግር የሀገር ውስጥ ፈጠራ መፍትሄዎችን ማጎልበት፣ በዓለምአቀፍ ኔትወርኮች የሃክቶን ፈጠራ ፈተናዎችን ልምድ ማሳደግ፣ ከአዳዲስ መሳሪያዎች እና ቴክኖሎጂዎች ጋር ማስተዋወቅን ያለመ ውድድር ነው።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበጎንደር ከተማ የክልሉ መንግሥት ያቀረበውን የሰላም ጥሪ ተቀብለው የተሀድሶ ሥልጠና የወሰዱ ወጣቶች ወደ ማኅበረሰቡ ተቀላቀሉ።
Next articleየሀራ ከተማ ነዋሪዎች በአካባቢያቸው ሰላም ዙሪያ እየመከሩ ነው።