
ባሕር ዳር: ግንቦት 28/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የጽንፈኛውን የጥፋት ዕቅድ ተቀብለው እና በሁኔታዎች ተደናግረው በተሳሳተ ተግባር ሲንቀሳቀሱ የነበሩ 69 ግለሰቦች የክልሉ መንግሥት የሰጠውን የሰላም ጥሪ ተቀብለው የተሀድሶ ሥልጠና በመውሰድ ወደ ማኅበረሰቡ ተቀላቅለዋል። በሥልጠና መድረኩ የተገኙት በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት መምሪያ ኀላፊው ግርማይ ልጅአለም የሁከት ፣ የግጭት እና የጦርነት አማራጭን በመጠቀም የሚፈታ የሕዝብ ጥያቄም ኾነ ችግር እንደማይኖር ገልጸዋል።
በዚህም ወጣቶች የክልሉ መንግሥት የሰጠውን የሰላም ጥሪ ተቀብለው ወደ ማኅበረሰቡ መቀላቀላቸው እና ወደ መደበኛ የሥራ ሁኔታ መመለሳቸው ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ ትልቅ ሚና አለው ብለዋል። በቀጣይ የቀረበውን የሰላም ጥሪ ያልተቀበሉ አካላት ጥሪውን በመቀበል ወደ ማኅበረሰቡ እንዲቀላቀሉ ጥሪ አቅርበዋል።
የጎንደር ከተማ አሥተዳደር የሰላም እና ጸጥታ መምሪያ ኀላፊ ኮማንደር አሰፋ ሽቤ እንደገለጹት ኾን ብለው ወይም ተደናግረው በተሳሳተ ተግባር ሲንቀሳቀሱ የነበሩ 69 የተሀድሶ ሠልጣኞች የክልሉ መንግሥት የሰጠውን የሰላም ጥሪ መቀበላቸውን እና ዘላቂ በኾነ ሰላማዊ መንገድ እንዲጓዙና የሰላም እና የልማት ተጠቃሚ እንዲኾኑ ከግንቦት 24/09/2016 ዓ.ም እስከ 25/09/2016 ዓ.ም ለሁለት ቀናት የተሀድሶ ሥልጠና መሰጠቱን ገልጸዋል።
የተሀድሶ ሥልጠና መድረኩ የክልሉ ትራንስፖርት እና ሎጅስቲክስ ባለሥልጣን ዋና ዳሬክተር ዘውዱ ማለደ የከተማው የብልጽግና ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ቻላቸው ዳኘው እና የከተማው ፖለቲካ ዘርፍ ኃላፊ ተስፋ መኮንን በተገኙበት ተሰጥቷል። በመድረኩ አሁንም ቢኾን በውጭ ያሉ የታጠቁ አካላት የያዙት አጀንዳ የሚጠቅም አለመኾኑ ሰፊ ውይይት ተደርጓል ነው የተባለው።
የተሰጠው ሥልጠና አቅም በመፍጠር ከሕዝቡ ጋር ተቀላቅለው ቤተሰቦቻቸውን የሚመሩበት እና ለጎንደር ከተማ እና ለዙሪያው ብሎም ለክልሉ ሰላም አስተዋጽኦ የሚያደርጉበትን መንገድ ለመፍጠር ታሳቢ ያደረገ የተሀድሶ ሥልጠና ስለመኾኑም ተጠቁሟል ።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
