
ባሕር ዳር: ግንቦት 27/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ከግንቦት 21/2016 ዓ.ም ጀምሮ ሲከናወን የቆየው የአዲስ አበባ አጀንዳ የማሠባሠብ የምክክር ምዕራፍ መጠናቀቁን የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ገልጿል። የኮሚሽኑ ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ በሰጡት መግለጫ ሂደቱ በስኬት መጠናቀቁን ገልጸዋል።
ከአዲስ አበባ 119 ወረዳዎች የተውጣጡ የማኅበረሰብ ክፍል ተወካዮች፣ የፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮች፣ የሕግ አውጪ፣ ተርጓሚ እና አስፈጻሚ አካላት የተለያዩ ማኅበራትን የወከሉ ተሳታፊዎች የአዲስ አበባን አጀንዳዎች አደራጅተው ለኮሚሽኑ አስረክበዋል። አጀንዳ የመስጠቱ ተግባር በሁሉም ተሳትፎ መከናወኑን ጠቅሰው በየመድረኩ ሃሳቦች ያለገደብ መንሸራሸራቸውን ተናግረዋል።
የተለያየ ሃሳብ ያላቸው አካላት በጋራ መወያየታቸውን ገልጸው ይህም የሃሳብ ልዩነቶችን በምክክር ለመፍታት የመጀመሪያው ምዕራፍ መኾኑንም ተናግረዋል። ኢፕድ እንደዘገበው ኮሚሽኑ አጀንዳዎችን በቅደም ተከተል ካስቀመጠ በኋላ ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ እንደሚያደርግ ጠቁመዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
