“የመንግሥት ሠራተኞች የተሰጣቸውን ሙያዊ ኀላፊነት በአግባቡ መወጣት አለባቸው” ድረስ ሳህሉ (ዶ.ር.)

67

ባሕር ዳር: ግንቦት 27/2016 ዓ.ም (አሚኮ)በወቅታዊ የሠላም፣ የልማት እና መልካም አሥተዳደር ጉዳዮች ዙሪያ በደብረ ማርቆስ ከተማ ከሚገኙ የመንግሥት ሠራተኞች ጋር ውይይት ተካሂዷል። የመንግሥት ሠራተኞች የመንግሥት ፖሊሲዎች እና ስትራቴጅዎች በአግባቡ እንዲፈጸሙ ሚናቸው ከፍተኛ ነው፡፡

የመንግሥት ሠራተኞች የተጣለባቸውን ሙያዊ ኅላፊነት እና ግዴታ በአግባቡ በመወጣት ለክልሉ ዘላቂ ሠላም እና ልማት መረጋገጥ የድርሻቸውን ማበርከት እንዳለባቸው በምክትል ርዕሰ መሥተዳድር ማዕረግ የገጠር ዘርፍ አሥተባባሪ እና የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ኀላፊ ድረስ ሳህሉ (ዶ.ር.) ገልጸዋል፡፡

አኹን ካለው ቀጣናዊ እና ዓለም አቀፋዊ ተጽእኖ ጋር ተዳምሮ የሠላም እጦቱ ክልሉን ለከፋ ጉዳት እንዳይዳርገው ከስሜታዊነት በጸዳ መንገድ የመንግሥት ሠራተኞች ለሠላም ቅድሚያ በመስጠት ኀብረተሰብን የማገልገል ኀላፊነታቸውን መወጣት እንዳለባቸውም አመላክተዋል፡፡ በቀጣይም በአካባቢው ዘላቂ ሠላም እንዲረጋገጥ መንግሥት ከማኀበረሰቡ ጋር ተቀራርቦ እንዲሠራ የጠየቁት የውይይቱ ተሳታፊች ሰላምን ለማምጣት ለሚደረገው ጥረት የድርሻቸውን እንደሚወጡም ተናግረዋል።

መሪዎች የውስጥ ክፍተቶቹን በመለየት በሕዝብ ዘንድ የሚነሱ የመልካም አሥተዳደር ጥያቄዎችን መፍታት ተቀዳሚ ተግባራቸው ሊኾን ይገባል ብለዋል የውይይቱ ተሳታፊዎች፡፡ የምስራቅ ጎጃም ዞን ኮማንድ ፖስት ሠብሳቢ እና በምዕራብ እዝ የ403ኛ ኮር አዛዥ ብርጋዴር ጀኔራል አዘዘው መኮንን በክልሉ ለተፈጠረው ግጭት መፍትሄ እንዲገኝለት በማኀበረሰቡ መካከል የእርስ በእርስ መተማመን መፍጠር ያስፈልጋል ብለዋል።

በቀጣይ ቀጣናው ከወንጀል ድርጊቶች ስጋት ነጻ ኾኖ ዘላቂ ሠላም እንዲረጋገጥ የመንግሥት ሠራተኛው የድርሻውን ሊያበረክት ይገባል ብለዋል። የልማት እና መልካም አሥተዳደር ሥራዎች በተሟላ መንገድ ለማከናወን ሠራተኞች ሕዝብ እና መንግሥት የሰጣቸውን ኀላፊነት በአግባቡ እንዲወጡ የደብረ ማርቆስ ከተማ አሥተዳደር ከንቲባ መንበሩ ዘውዴ ጠይቀዋል። ጉድለት ያለባቸውን መሪዎች በማስተካከል ችግሮችን ለመፍታት ከማኀበረሰቡ ጋር በጋራ እየተሠራ ስለመኾኑም ጠቁመዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“የፍትሕ ጉባኤ የፍቅር ሱባኤ…”
Next articleበአዲስ አበባ የአጀንዳ ማሠባሠብ የምክክር ምዕራፍ ተጠናቀቀ።