
ባሕር ዳር፡ መጋቢት 11/2012 ዓ.ም (አብመድ) በኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት በተፈጠረው መደናገጥ የደም ለጋሾች ቁጥር መቀነሱ እንዳሳሰበው የባሕር ዳር ደም ባንክ አገልግሎት አስታውቋል፡፡
የባሕር ዳር ደም ባንክ አገልግሎት ኃላፊ አቶ ምክሩ ሽፈራው ለአብመድ እንደተናገሩት አብዛኛውን ጊዜ የደም ልገሳ የሚከናወንባቸው ቦታዎች እንደ ዩኒቨርሲቲዎች፣ትልልቅ ፋብሪካዎች እና የመንግስት ተቋማት ናቸው፡፡ እነዚህ ተቋማት ደግሞ ከኮሮና ቫይረስ ጋር በተያያዘ በተላለፈው መመሪያ ምክንያት እንቅስቃሴያቸው ከወትሮው በተለዬ ሁኔታ ተገትቷል፡፡ በዚህም ምክንያት ከዚህ በፊት በየቀኑ ከ300 እስከ 400 ከረጢት ደም ይሰበስብ የነበረው የደም ባንኩ ከሰሞኑ እስከ አራት ከረጢት ደም ወርዷል ብለዋል አቶ ምክሩ፡፡
በመሆኑም የደም ባንኩ አሁን ደም ለሚያስፈልጋቸው ታካሚዎች እያቀረበ ያለው ከሁለት ሳምንታት በፊት የሰበሰበውን መሆኑን ነው የነገሩን፡፡ የደም ባንኩ እስከ ሁለት ሳምንታት የሚሆን ደም ካልሆነ በስተቀር ሌላ እንደሌለው የገለጹት አቶ ምክሩ ችግሩ የሚቀጥል ከሆነ ከፍተኛ የደም እጥረት እንደሚፈጠር ስጋታቸውን ገልጸዋል፡፡ በዚህም የተነሳ ነው ኮሮና ቫይረስ ከሚያደርሰው ጥፋት በላይ የደም እጥረቱ በሰዎች ላይ የከፋ ችግር ሊያደርስ ይችላል ያሉት፡፡
ችግሩን ለመፍታትም ቋሚ የደም ባንክ ባለባቸው እንደ ባሕርዳር ቀበሌ 15 አካባቢ፣ ጎንደር፣ ደሴ እና ሌሎች ጣቢያዎች ላይ ኅብረተሰቡ ደም በመስጠት እንዲተባበር ኃላፊው ጥሪ አቅረበዋል፡፡
በሌላ በኩል ዩኒቨርሲቲዎች፣ ትልልቅ ፋብሪካዎች እና የመንግስት ተቋማት ችግሩን በመገንዘብ የደም ባንክ አገልግሎት ሰራተኞች ከለጋሾች ደም እንዲሰበስቡ ፈቃድ እንዲሰጡ ጠይቀዋል፡፡
አሁን ላይ ወደ የትኛውም ተቋም ገብቶ እንደ ከዚህ ቀደሙ ደም ለመሰብሰብ ችግር እንደሆነባቸው የገለጹት አቶ ምክሩ ለኮሮና ቫይረስ የሚሰጠው ትኩረት ጥሩ ቢሆንም በሆስፒታሎች አስቸኳይ ደም የሚፈልጉ ወላድ እናቶች፣ የመኪና አደጋ የገጠማቸው ዜጎች እና ሌሎችም ቀዶ ህክምና የሚያስፈልጋቸው በመኖራቸው አንዱን ገድሎ አንዱን ማዳን እንዳይሆን በጥንቃቄ ደም የሚሰበሰብበትን ሁኔታ የተቋማት ኃላፊዎች ቢያመቻቹ የተሻለ እንደሚሆን ነው ያስገነዘቡት፡፡
አሁን ያለው የኮሮና ቫይረስ ችግርን ለመፍታት የተወሰደው ርምጃ ለሁለት ሳምንታት እንኳን ይራዘም ቢባል ኮሮና ከሚገድለው ሰው በላይ በደም እጦት የሚሞተው ሊበልጥ እንደሚችል ግምታቸውን ተናግረዋል፡፡ እንደ ሰቆጣ ባሉ አካባቢዎች ከአሁኑ የደም እጥረት እንደተፈጠረና በዚህም የተነሳ ወደ መቀሌ “ሪፈር” እያሉ መሆኑን ነው የነገሩን፡፡ ካለው የደም እጥረት አንጻር የቀዶ ህክምና ሥራዎች ለሁለት ወራት እንዲራዘሙ የማድረግ መፍትሄዎች እየተወሰዱ መሆኑን፤ ይህ የሆነውም ካለው ችግር አንጻር በመሆኑ መፍትሔ እንዲገኝ ኅብረተሰቡ ደም የመለገስ ልምዱን እንዲያስቀጥል ነው የጠየቁት፡፡
እማዋይሽ ልንገረው እና ጀማል ሀሰን የተባሉ ደም በመለገስ የሚታወቁ የባሕርዳር ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች እንደነገሩን ደግሞ አሁንም ቢሆን ደም ለመስጠት ፍላጎት አላቸው፡፡ ሆኖም ሁኔታው ስላልተመቸ መስጠት አልቻሉም፤ እናም ደም ለመለገስ ምቹ ሁኔታ በግቢያቸው እንዲፈጠር ጠይቀዋል፡፡
ዘጋቢ፡-ምሥጋናው ብርሃኔ