“መነሻየን እያሰብኩ ነው የምሠራ” ባለሃብቱ በላይነህ ክንዴ

146

ባሕር ዳር: ግንቦት 27/2016 ዓ.ም (አሚኮ)በላይነህ ክንዴ ግሩፕ በደብረ ብርሃን ከተማ ያስገነባው ፊቤላ ኢንዱስትሪያል የመኪና መገጣጠሚያ ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ እንዲሁም የክልሉ እና የፌዴራል ከፍተኛ መሪዎች በተገኙበት ተመርቋል። በምረቃ ሥርዓቱ ላይ የበላይነህ ክንዴ ግሩፕ መሥራች እና የቦርድ ሠብሣቢ በላይነህ ክንዴ የተመረቀው መኪና መገጣጠሚያ በጥራት፣ በፍጥነት እና በልዩ ትኩረት የተሠራ መኾኑን ገልጸዋል።

መገጣጠሚያው ከሚኒባስ ጀምሮ ትልልቅ አውቶብሶችን ጭምር በመገጣጠም ለገበያ ማቅረብ የሚያስችል ነው ብለዋል። መገጣጠሚያው በዓመት ውስጥ 1 ሺህ በኤሌክትሪክ የሚሠሩ ተሽከርካሪዎችን የማምረት አቅም እንዳለውም ገልጸዋል። በዚሁ መገጣጠሚያ የተሠሩ ግዙፍ የኤሌክትሪክ አውቶብሶች በአዲስ አበባ ውስጥ ለሕዝብ መጓጓዣነት እያገለገሉ እንደሚገኙም ጠቁመዋል።

ምቾት እና ዘመናዊነታቸው ጥሩ የሕዝብ ተቀባይነት ያገኘ እንደኾነም ገልጸዋል። አቶ በላይነህ “መነሻየን እያሰብኩ ነው የምሠራ” ሲሉም ተናግረዋል። “ማጣት እና ድህነት የሚፈጥረውን ችግር እገነዘበዋለሁ፣ ኑሬበትም አውቀዋለሁ፤ በታታሪነት መሥራት ከራስም በላይ ሀገርን ከድህነት ነጻ እንደሚያወጣ እሙን ነው” ሲሉ ገልጸዋል።

በሺህዎች የጀመሩትን ሥራ በትኩረት በመሥራታቸው አሁን ላይ በብዙ ቢሊዮኖች እንዳደረሱትም ተናግረዋል። ችግር እና ውጣ ውረድን ታግለው በማሸነፍ ለስኬት እንደበቁ የገለጹት ባለሃብቱ ዛሬ ላይ ከራሳቸውም አልፈው ለሀገር በሚተርፍ ኢንቨስትመንት እየሠሩ ነው። ከመኪና መገጣጠሚያ በተጨማሪ በሌሎች ትላልቅ አምራች ኢንዱስትሪዎች ላይ በመሳተፍ በተለይም ሕዝብን እየፈተነ የሚገኘውን የኑሮ ውድነት ለማቃለል በትኩረት እየሠሩ እንደሚገኙም ጠቅሰዋል።

አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ ለማድረግ በማሰብም የቅባት ሰብሎችን የሚፈጭ እና ዘይት በስፋት ለማምረት የሚያስችል ማሽን በቅርብ ቀን መትከላቸውን ገልጸዋል። ከዚህ በፊት ብዙው የዘይት ጥሬ እቃ ከውጭ እንደሚመጣ ገልጸው ከዚህ በኋላ ግን የአርሶ አደሮችን ሰብል ቀጥታ በመቀበል እና በመፍጨት ዘይት ለማምረት ምቹ ሁኔታ መፈጠሩን ተናግረዋል። ከራስ አልፎ ለሀገር እና ለትውልድ መሥራት ያስፈልጋል፤ በመደጋገፍ፣ በመረዳዳት እና በመመካከር ልማትን መሥራት እና ሕዝብን ከድህነት በዘላቂነት ማላቀቅ አለብን ሲሉም ባለሃብቱ ተናግረዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየደሴ ከተማ አሥተዳደር በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ከከተማዋ ወጣቶች ጋር መከረ።
Next articleበአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የነበሩ 200 ኢትዮጵያውያን ወደ ሀገራቸው ተመለሱ።