
ደሴ: ግንቦት 27/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በመድረኩ የግብርና ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ መለስ መኮንን (ዶ.ር)፣ የአማራ ክልል መንግሥት ተጠሪ አየነ ብርሃን እና የደሴ ከተማ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ሳሙኤል ሞላልኝ ተገኝተዋል። ደሴ ከተማ ሰላሟን አስጠብቃ የተለያዩ መሠረተ ልማቶችን እየሠራች ያለች ከተማ መኾኗን እና ለዚህ ደግሞ የወጣቱ ሚና ከፍተኛ ስለመኾኑ በመድረኩ ተነስቷል።
የመድረኩ ተሳታፊ ወጣቶች ከተማ አሥተዳደሩ ስለሚሠራቸው መሠረተ ልማቶች ምሥጋናቸውን አቅርበዋል። የከተማዋን ሰላም በማስጠበቅ ረገድ ወጣቱ የራሱን ድርሻ ሊወጣ እንደሚገባም ተናግረዋል። የደሴ ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ሳሙኤል ሞላልኝ የመድረኩ ዋና ዓላማ የከተማዋን ሰላም አስጠብቀን በልማት እና በመልካም አሥተዳደር ዙሪያ ከወጣቱ ጋር ለመምከር ነው ብለዋል።
የተሠሩ ሥራዎችን በተመለከተ ውይይት በማድረግ ከመሪዎች እና ከኅብረተሰቡ ምን ይጠበቃል የሚለውን ጉዳይ ለማስገንዘብ እንደሚያግዝ ነው ያስረዱት። ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው የከተማዋን ሰላም አስጠብቆ ልማትን ለማፋጠን ከወጣቱ ጋር ስምምነት ላይ ስለመደረሱም ገልጸዋል፡፡ ከተማ አሥተዳደሩ ከወጣቶቹ የተነሱትን የመልካም አሥተዳደር ጥያቄዎች ተቀብሎ በቀጣይ ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሠራባቸውም ተናግረዋል፡፡
ዘጋቢ፦ ፊኒክስ ኃየሎም
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
