
ባሕር ዳር: ግንቦት 27/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በአዲስ አበባ እየተካሄደ ባለው በሀገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ የአጀንዳ ልየታ ላይ ተሳታፊዎች ሀገራዊ ችግሮቻችንን በግልጽ ለይተናል ብለዋል። በምክክሩ ላይ የኅብረተሰብ ተወካይ ኾነው ተሳታፊ የኾኑት ለይላ ሀሰን የጋራ ሀገር ለመገንባት ትልቅ ተስፋ የሚጣልበት ምክክር መኾኑን ገልጸዋል።
የአጀንዳ ማሠባሠብ እና ልየታው ከእኔ ወደ እኛ ሀሳብ ያሸጋገረ ነው ያሉት ለይላ ሀሰን በሂደቱም “ሁላችንም ተወካዮች በነጻነት ሃሳባችንን ገልጸናል” ብለዋል። በዚህ የምክክር ሂደት ውስጥ ምክክር እና ውይይት የችግሮች ሁሉ መፍቻ ቁልፍ መኾኑን በተግባር ተመልክተናልም ብለዋል። ሌላኛው የኅብረተሰብ ተወካይ መርጊያ በቀለ ባለፉት ቀናት በነበረው ምክክር እና አጀንዳ ልየታ የተለያየ ሃሳብ ያላቸው ሰዎች ተሳታፊ መኾናቸውን ተናግረዋል።
በምክክሩም ላይ “ችግሮች ናቸው ያልናቸውን ሃሳቦች በሙሉ አንስተናል” ያሉት መርጊያ በቀለ ይህም በምክክሩ ሂደት አንዱ ግብ ሲኾን ለነገው ትውልድ የምናስተላልፋት ሀገር ከትናንት ቁርሾ እና ቂም የፀዳች እንዲሁም የበለጸገች እንድትኾን የሚረዳ ይኾናል ብለዋል። ኢቢሲ እንደዘገበው በዚህ ምክክር “ተስፋ እንዲኖር እና የሕዝቦች መተማመን ብሎም የጋራ አጀንዳ ያላት ሰላማዊት ሀገር እንድትኖረን እንጠብቃለን” ነው ያሉት።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
