“ባለፉት 10 ወራት 330 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር ካፒታል ላስመዘገቡ አልሚዎች ፈቃድ ተሰጥቷል” አቶ እንድሪስ አብዱ

32

ደብረ ብርሃን፡ ግንቦት 27/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የ2016 ዓ.ም ኢትዮጵያ ታምርት ክልላዊ የማጠቃለያ መርሐ ግብር በደብረብርሃን ከተማ እየተካሄደ ነው። በመርሐ ግብሩ መጀመሪያ ላይ በበላይነህ ክንዴ ግሩፕ የተገነባው የመኪና መገጣጠሚያ ተመርቋል። የአማራ ክልል ኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት ቢሮ ኀላፊ እንድሪስ አብዱ የመኪና መገጣጠሚያው ግንባታ በአጭር ጊዜ ተጠናቅቆ ፍሬ ያፈራ ነው ብለዋል።

ዘላቂ እድገትን ለማረጋገጥ የአምራች ኢንዱስትሪዎች ማደግ እና መስፋፋት ወሳኝ ሚና እንዳለውም ቢሮ ኀላፊው ገልጸዋል። የኢንዱስትሪዎች መስፋፋት የከተሞችን እድገት ጭምር እንደሚያፋጥንም ጠቁመዋል። ይህንን ተከትሎም የሕዝቡ የዕለት ከዕለት ኑሮ የተሻለ ለውጥ እንዲያመጣ ያስችላል ነው ያሉት።

አቶ እንድሪስ የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ከተጀመረ ወዲህ በርካታ ተጨባጭ ለውጦች እየመጡ እንደኾነም ተናግረዋል። ለአብነትም በክልሉ ውስጥ በተለያዩ ምክንያቶች ለረጅም ዓመታት ምርት አቁመው የነበሩ 329 መካከለኛ እና ከፍተኛ አምራች ኢንዱስትሪዎች ወደ ማምረት መመለሳቸውን ጠቅሰዋል። የዘርፉን የአሠራር ክፍተቶች ለማረም ጥረት መደረጉንም ጠቁመዋል። ወደ ውጭ የሚላኩ ምርቶችን እና ተኪ ምርቶችንም የሚያመርቱ ኢንዱስትሪዎች ቁጥር እያደገ ስለመኾኑም ተናግረዋል።

ቢሮ ኀላፊው “ባለፉት 10 ወራት 330 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር ካፒታል ላስመዘገቡ 2ሺህ 260 አልሚዎች ፈቃድ ተሰጥቷል” ሲሉም ተናግረዋል። አልሚዎች ያቀረቧቸው ፕሮጀክቶች ተቀባይነት አግኝተው ግምገማውን ላለፉ 376 አምራች እና ለሌሎችም ዘርፎች በአጠቃላይ 5 ሺህ 855 ሄክታር መሬት መተላለፋንም ጠቅሰዋል። በዚህም ለ385 ሺህ ዜጎች የሥራ እድል ለመፍጠር ታቅዶ እየተሠራ ነው።

የአምራች ኢንዱስትሪውን የፋይናንስ ማነቆ ለመፍታት ከፋይናንስ ተቋማት ጋር በመተባበር እየተሠራ ነው ብለዋል። በዚህም ለ515 ኢንዱስትሪዎች በሊዝ ፋይናንስ ሥራ ማሥኬጃ 16 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር እንዲቀርብ ተደርጓል። እንደ ቢሮው ኀላፊው ገለጻ 267 አምራች ኢንዱስትሪዎች 318 ሺህ 167 ተኪ ምርቶችን በማምረት 641 ነጥብ 8 ሚሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሬ ማዳን ችለዋል። 33 አምራች ኢንዱስትሪዎች ደግሞ 104 ሺህ 838 ቶን ምርት ወደ ውጭ በመላክ 82 ነጥብ 2 ሚሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሬ ማስገኘታቸውን ገልጸዋል።

ዘርፉ አበረታች ውጤቶች የታዩበት ቢኾንም አሁንም ቢኾን የአገልግሎት አሰጣጡ በሚፈለገው ደረጃ አለመድረሱን አቶ እንድሪስ አብራርተዋል። መሬት አጥረው የተቀመጡ፣ የተሰጣቸውን መሬት በባንክ አስይዘው የጠፉ እና የኢንቨስትመንት መሬቶችን ከተሰጣቸው አላማ ውጭ የሚጠቀሙ ባለሃብቶች ቁጥር መበራከቱ የዘርፉ ፈተናዎች ኾነው ተነስተዋል። የኃይል እና የፋይናንስ አቅርቦት በሚፈለገው ልክ አለማደጉም እንደእንቅፋት ኾነው ተገልጸዋል። እነዚህን የዘርፉ ተግዳሮቶች ለመፍታት በዚህ ዓመት የተደረጉ የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄዎች ከፍተኛ ሚና እንደሚኖራቸውም አቶ እንድሪስ ተናግረዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው ሲላኦም ማዕከልን ጎበኙ።
Next article“በአጀንዳ ልየታው ችግሮቻችንን በግልጽ ለይተናል” ሲሉ የማኅበረሰብ ተወካዮች