
ባሕር ዳር: ግንቦት 27/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የ2016 ዓ.ም የኢትዮጵያ ታምርት ክልላዊ የማጠቃለያ መርሐ ግብር ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደን ጨምሮ ሌሎች የክልሉ እና የፌዴራል መንግሥት ከፍተኛ መሪዎች፣ አልሚ ባለሃብቶች እና የሚመለከታቸው ባለሙያዎች በተገኙበት እየተካሄደ ነው።
ከፍተኛ መሪዎቹ በከተማዋ የተገነባውን ግዙፍ የመኪና መገጣጠሚያ ፍብሪካ ከመረቁ በኋላ ለ2016 ዓ.ም የኢትዮጵያ ታምርት ክልላዊ ንቅናቄ የማጠቃለያ መርሐ ግብር የተዘጋጀውን የፋብሪካ ምርቶች አውደ ርዕይ ጎብኝተዋል። ዐውደ ርዕዩን ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ ከፍተውታል።
የኢትዮጵያ ታምርት መርሐ ግብር መንግሥት የአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፉን ችግሮች ለማቃለል እየተገበራቸው ከሚገኙ የመፍትሔ ዕርምጃዎች መካከል አንዱ ነው ተብሏል። መርሐ ግብሩ በ2014 ዓ.ም ይፋ የተደረገ ሲኾን ለተከታታይ 10 ዓመታት እስከ 2023 ዓ.ም ይተገበራል። የኢትዮጵያ ታምርት መርሐ ግብር የ10 ዓመቱን የልማት ግቦች ለማሳካት አንዱ መንገድ ኾኖም እንደ ሀገር እየተሠራበት ነው።
የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ በአማራ ክልል በተለያዩ ዞኖች እና ወረዳዎች ሲካሄድ መቆየቱም ይታወሳል። የክልሉ ኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት ቢሮ መረጃ እንደሚያመላክተው ንቅናቄው በ2016 ዓ.ም በ12 ዞኖች እና በ50 ወረዳዎች ሲካሄድ ቆይቷል። ንቅናቄው በዘርፉ የሚያጋጥሙ ችግሮችን በመፍታት እና እድሎችን በመፍጠር ለኢኮኖሚው መዋቅሯዊ ሽግግር የበኩሉን አስተዋጽኦ ሲወጣ መቆየቱም ተጠቁሟል። በደብረ ብርሃን ከተማ በተዘጋጀው የኢትዮጵያ ታምርት ማጠቃለያ መርሐ ግብር ላይ ባለድርሻ አካላት የሚሳተፋበት የውይይት መድረክም እንደሚካሄድም ተጠቁሟል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
 
             
  
		