“ባለሃብቶች በወሰዱት መሬት ላይ ፈጥነው በማልማት ራሳቸውን፣ ሕዝብን እና ሀገርን ተጠቃሚ በሚያደርግ ተግባር ላይ መሰማራት አለባቸው” ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ

57

ደብረ ብርሃን፡ ግንቦት 27/2016 ዓ.ም (አሚኮ)

በበላይነህ ክንዴ ግሩፕ የተገነባውን የፊቤላ ኢንዱስትሪያል መኪና መገጣጠሚያ ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ እና ሌሎችም የክልል እና የፌዴራል ከፍተኛ መሪዎች በተገኙበት ተመርቋል። ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ በላይነህ ክንዴ ግሩፕ ተግባራዊ እያደረጋቸው የሚገኙት አምራች ኢንዱስትሪዎች ለሀገር ከፍተኛ ፋይዳ ያላቸው መኾናቸውን ጠቁመዋል። ኢንዱስትሪዎች ተኪ ምርቶችን በማምረት የኑሮ ውድነትን እየቀነሱ እና ሕዝብን ተጠቃሚ እያደረጉ ስለመኾኑም ርእሰ መሥተዳድሩ ገልጸዋል።

ዛሬ በደብረብርሃን ከተማ የተመረቀው የመኪና መገጣጠሚያም የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን በመገጣጠም የመጓጓዣ ኢንዱስትሪውን የሚያዘምን ነው ብለዋል። ከዚህም በተጨማሪ ለበርካታ ዜጎች የሥራ ዕድል የፈጠረ እና የቴክኖሎጅ ሽግግርም እያደረገ የሚገኝ ፋብሪካ ነው ብለዋል። ርእሰ መሥተዳድሩ ይህንን ግዙፍ ፋብሪካ በፍጥነት እና በጥራት ገንብተው እውን ያደረጉትን ባለሃብት በላይነህ ክንዴን አመሥግነዋል። “ለሕዝብ እና ለሀገር የሚሠራ ባለሃብት በታሪክም የተመሠገነ ነው፤ አቶ በላይነህ የወሰደውን መሬት አጥሮ በማስቀመጥ የማይታወቅ፣ ግዙፍ ኢንዱስትሪዎችን በመገንባት አርዓያ የኾነ እና በርካታ ዜጎችን የሚደግፍ የሀገር ባለውለታ ነው” ብለዋል ርእሰ መሥተዳድሩ።

ባለሃብቶች በወሰዱት መሬት ላይ ፈጥነው በማልማት ራሳቸውን፣ ሕዝብን እና ሀገርን ተጠቃሚ በሚያደርግ ተግባር ላይ መሰማራት እንዳለባቸውም መልዕክት አስተላልፈዋል። ርእሰ መሥተዳድሩ በሰሜን ሸዋ ዞን በተለይም ከቱለፋ እስከ ደብረብርሃን ባለው አካባቢ ከፍተኛ የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ እንዳለ ጠቁመዋል። ኢንዱስትሪዎች ሲገነቡ ነገን ታሳቢ ያደረጉ እና ጤናማ የከተሞች መስፋፋት እንዲኖር ታሳቢ ያደረጉ እንዲኾኑ የየአካባቢው መሪዎች እና ባለሃብቶች በትኩረት መሥራት አለባቸው ብለዋል።

ርእሰ መሥተዳድሩ ሕዝብን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ትልልቅ ልማቶችን ጀምሮ ለማጠናቀቅ ሰላም ወሳኝ ሚና እንዳለውም ጠቁመዋል። ማኅበረሰቡ ሰላም እና አንድነቱን ማስጠበቅ፣ የተገነቡ ልማቶችንም መንከባከብ ይገባዋል ሲሉ መልዕክት አስተላልፈዋል። መንግሥት ምንጊዜም ቢኾን ሰላምን አጥብቆ እንደሚሻ እና ለዚህም ሲባል በግጭት ውስጥ ያሉትን አካላት ሁሉ በሰላማዊ መንገድ እንደሚቀበል ገልጸዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየፖለቲካ ፓርቲዎች በምክክሩ በመሳተፍ ታሪካዊ ዐሻራቸውን ማኖር እንዳለባቸው ተገለጸ።
Next articleየ2016 ዓ.ም ኢትዮጵያ ታምርት ክልላዊ የማጠቃለያ መርሐ ግብር በደብረ ብርሃን ከተማ እየተካሄደ ነው።