የፖለቲካ ፓርቲዎች በምክክሩ በመሳተፍ ታሪካዊ ዐሻራቸውን ማኖር እንዳለባቸው ተገለጸ።

13

ባሕር ዳር: ግንቦት 27/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በሀገራዊ ምክክሩ የፖለቲካ ፓርቲዎች በመሳተፍ ታሪካዊ አሻራቸውን ማኖር እንዳለባቸው የአዲስ አበባ የአጀንዳ ማሰባሰብ የምክክር ምዕራፍ ተሳታፊዎች ገለጸዋል። የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ) ተወካይ አቶ ግርማ ሰይፉ ሀገራዊ ምክክር በየዓመቱ የሚደረግ ነገር ባለመኾኑ በሂደቱ ተሳታፊ ያልኾኑ የፖለቲካ ፓርቲዎች በምክክሩ በመሳተፍ አሻራቸውን ማኖር አለባቸው ብለዋል።

እንደ ኢዜማ በሀገራዊ ምክክሩ ስንሳተፍ ዋነኛው አላማችን ሀገር በዘላቂ መሰረት ላይ እንድትቆምና በማያግባቡን ዋና ዋና ጉዳዮች ላይ ከስምምነት እንድንደርስ በማሰብ ነው ያሉት አቶ ግርማ የፖለቲካ ፓርቲዎች የፖሊሲ አጀንዳዎችን እና የሀገራዊ ምክክር አጀንዳዎችን ለይቶ ማየት እንደሚጠበቅባቸው ተናግረዋል።

እንደ አቶ ግርማ ገለጻ እንደ ሀገር ሀገራዊ ምክክሩ መደረጉ ትልቅ ርምጃ ነው። አኹን ምክክሩ ባለበት የአጀንዳ አሰባሰብ ደረጃ በመወያየት አጀንዳ እየተለየ መኾኑን አመላክተው በምን ጉዳይ ላይ እንደ ሕዝብ መወያየት እንዳለብን ማወቅ መቻላችን በራሱ ትልቅ ነገር ነው ብለዋል። ታሪካዊ ኃላፊነት የተሰጠው ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኃላፊነቱን በሚገባ እንደሚወጣ እምነት እንዳላቸው የተናገሩት አቶ ግርማ ኮሚሽኑ የተወሰኑ መንገዶችን ልንሻገርበት የምንችልበትን ሀዲድ መዘርጋት ከቻለ በራሱ ትልቅ ስኬት መኾኑን ጠቁመዋል።

ታዋቂ ግለሰቦች፣ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች እንዲኹም የተለያዩ አካላት ተሰባስበው ሀገራዊ በኾኑ ጉዳዮች ላይ እየተወያዩ መኾኑ ትልቅ አጋጣሚ መኾኑን ተናግረው፤ የሀገራችን ችግሮች በውይይት መታወቁ መልካም ነው ብለዋል። ሌላኛው ሃሳባቸውን የሰጡት ተሳታፊ ሙሉጌታ ደበበ (ዶ.ር.) ለ50 ዓመታት ገደማ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ተሳትፎ እንደነበራቸው ገልጸው አሁን እንደ ሀገር ያሉትን ችግሮች ተቀምጦ መወያየት መቻል ያልተለመደ እና መልካም እድል መኾኑን ተናግረዋል።

ጦርነት በኢትዮጵያ ፖለቲካ ተሞክሮ ለውጥ አለማምጣቱን አስታውሰው ያሉትን ችግሮች በጠብመንጃ ሳይኾን በጠረጴዛ ዙሪያ በውይይት መፍታት አለብን ብለዋል። ሁሉም ዜጋ በምክክሩ በመሳተፍ የበኩሉን አስተዋጽኦ ማድረግ እንዳለበትም ገልጸዋል። ሕዝብ ጦርነት በቃን ብሎ ከሀገራዊ ምክክሩ ትልቅ ውጤት እየጠበቀ መኾኑን የጠቆሙት ሙሉጌታ (ዶ.ር.) እየተሳተፍኩበት ባለው የአዲስ አበባ የአጀንዳ ማሰባሰብ የምክክር ጉባዔ ምክክሩ በጥሩ ኹኔታ እተከናወነ በመኾኑ የሚጠበቀው ውጤት ይገኛል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ ብለዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበከተማ ግብርና ልማት የተሻለ ውጤት እየተመዘገበ መኾኑን የሰቆጣ ከተማ አሥተዳደር ግብርና ጽሕፈት ቤት አስታወቀ።
Next article“ባለሃብቶች በወሰዱት መሬት ላይ ፈጥነው በማልማት ራሳቸውን፣ ሕዝብን እና ሀገርን ተጠቃሚ በሚያደርግ ተግባር ላይ መሰማራት አለባቸው” ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ