ደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ኮሮና ቫይረስን ለመከላከል ጥንቃቄ እያደረገ መሆኑን አስታወቀ፡፡

948

ባሕር ዳር፡ መጋቢት 11/2012 ዓ.ም (አብመድ) ዓለም አቀፍ የጤና ስጋት የሆነውን ኮሮና ቫይረስ ለመከላከል የቅድመ ጥንቃቄ ሥራዎችን እየሠራ መሆኑን ደብረ ማርቆስ ዩኒቨርስቲ አስታወቀ፡፡

ደብረ ማርቆስ ዩኒቨርስቲ ኮሮና ቫይረስን ለመከላከል የሚያስችል የቴክኒክ ኮሚቴ በማቋቋም ሥራ ጀምሯል፡፡ በክፍል ውስጥ የሚፈጠርን ጥግግት ለማስቀረትና የተማሪዎች ጤንነት እንዲጠበቅ በማሰብም ትምህርታቸውን በኢሜል እና በሞጁል እንዲከታተሉ እያደረገ መሆኑን አስታውቋለ፡፡ አሁን ላይ ተማሪዎች ከዩኒቨርስቲው ግቢ መውጣትም ይሁን መግባት አይችሉም፡፡ በቤተ መጻሕፍት ውስጥም ይሁን በግቢው የሚያደርጉት እንቅስቃሴም በተናጠል ነው፡፡

አስተያዬታቸውን ለአብመድ የተናገሩ ተማሪዎችም ደኅንነታቸውን ለመጠበቅ ዩኒቨርሲቲው የወሰደውን እርምጃ ይደግፋሉ፡፡ ቫይረሱ ከሰው ወደ ሰው እንዳይተላለፍ ጤና ሚኒስቴር ያወጣቸውን መመሪያዎች እየተገበሩ ጥናታቸውንም እየቀጠሉ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

ደብረ ማርቆስ ዩኒቨርስቲ የኮሮና ቫይረስን አስመልክቶ ተማሪዎች በቂ መረጃ አግኝተው የራሳቸውን ንጽህና እንዲጠብቁ ለማስቻል በበራሪ ወረቀቶችና መልዕክቶችን በመቅረጽ እያሰራጨ ነው፡፡ በመኪና እየዞሩ ስለ ወረርሽኙ ግንዛቤ እየፈጠሩ እንደሆነም አብመድ ታዝቧል፡፡ የዩኒቨርሲቲውን የማኅበረሰብ ኤፍ ኤም ሬድዮ በመጠቀምም መልእክት እየተላለፈ ነው፡፡

የዩኒቨርሲቲው የሕዝብ ግንኙነትና የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር ግርማው አሸብር እንደተናገሩትም የተማሪዎችን ደኅንነት በመጠበቅ የመማር ማስተማር ተግባሩን በሰላማዊ መንገድ ለማስቀጠል የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ባስቀመጠው አቅጣጫ መሠረት ኮሚቴ ተቋቁሞ በትኩረት እየተሠራ ነው፡፡ ተማሪዎች ከግቢ መውጣትም ሆነ መግባት እንደማይችሉ እና ከግቢ ውጭ የሚመገቡ ተማሪዎች እንዳይቸገሩ በግቢው ውስጥ ካፌ በማዘጋጀት እዚያው እንዲመገቡ አቅጣጫ መቀመጡንም ተናግረዋል፡፡

ወላጆችም ይህንን ተገንዝበው ስጋት ሳይገባቸው ለተግባራዊነቱ እንዲተባበሩ አቶ ግርማው ጠይቀዋል፡፡ ተማሪዎቹ ንጽህናቸውን የሚጠብቁበት ቁሳቁስ እየቀረበ ይገኛል፡፡ ይህም ሆኖ ወረርሽኙ ቢከሰት ወደ ሌሎች ተማሪዎች እንዳይዛመት የማቆያ ህንጻ መዘጋጀቱን ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡

ዘጋቢ፡-ሰለሞን ጥበቡ

Previous articleሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን በኮሮና ቫይረስ ምክንያት የአስተዳደር ፍርድ ቤቶችን በከፊል ዘጋ፡፡
Next articleየኮሮና ስጋት ሌላ አስከፊ ሞት አንዳያስከትል ደም ባንክ ስጋቱን ገለጸ፡፡