
ሰቆጣ: ግንቦት 27/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ወይዘሮ አሰገደች የግሌ ይባላሉ። በሰቆጣ ከተማ 01 ቀበሌ ነዋሪ ናቸው። ከሦስት ዓመት በፊት በጀመሩት የከተማ ግብርና ልማት አትክልት እና ፍራፍሬ ጓሯቸውን እያለሙ ይገኛሉ። በዚህም ከራሳቸው አልፈው ለገበያ በማቅረብ ቤተሰባቸውን እያሥተዳደሩ እንደኾነ ገልጸዋል። በከተማ ግብርና ልማት መሥራት ‘ሁሉ በቤትህ’ እንዲኾን ያደርጋልም ይላሉ።
ለማልማትም ሰፊ ቦታ ሳይኾን የሥራ ፍላጎት ያስፈልጋል የሚሉት ወይዘሮ አሰገደች የግብርና ባለሙያዎች የሚሰጧቸው ድጋፍ ለውጤታማነት እንዳገዛቸው ተናግረዋል። የሰቆጣ ከተማ 01 ቀበሌ ግብርና ባለሙያ ወይዘሮ ገነት ፍስሃ ሴቶች በከተማ ልማት ከተሠማሩ ውጤታማነታቸው ከፍ ያለ እንደሚኾን አስገንዝበዋል።
ከሙያዊ ድጋፍ ባሻገር የግብዓት ድጋፍ እንደሚያስፈልጋቸውም ገልጸዋል። በቀጣይም አስፈላጊው ድጋፍ እንደሚደረግ ጠቁመዋል። በከተማ ግብርና ልማት ከ500 በላይ ሰዎችን ተጠቃሚ አድርገናል ያሉት የሰቆጣ ከተማ አሥተዳደር ግብርና ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ፍቅሩ ኀይሉ በጊዜያዊ እና በቋሚ አትክልት ጥሩ ጅማሮ እንዳለ ጠቁመዋል።
በቀጣይም አስፈላጊውን ድጋፍ በማድረግ የከተማ ግብርና ልማትን ለማልማት እንደሚሠሩ የገለጹት ኀላፊው የከተማ ልማትን ለሚያለሙ ሴቶችም ልዩ ድጋፍ እንደሚያደርጉ ገልጸዋል።
ዘጋቢ፦ ደጀን ታምሩ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
