
ባሕር ዳር: ግንቦት 27/2016 ዓ.ም (አሚኮ)በሳዑዲ አረቢያ የንግድ ምክር ቤት ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት የተመራ 79 አባላትን የያዘ የሳዑዲ አረቢያ የኢንቨስትመንት እና የንግድ ልዑካን ቡድን ኢትዮጵያን ሊጎበኝ መኾኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ነብዩ ተድላ ገልጸዋል። ጉብኝቱ የሁለቱን ሀገራት ኢኮኖሚያዊ ትስስር ለማጠናከር ዓላማ ያደረገ መኾኑን ነው አምባሳደር ነብዩ ያብራሩት።
የልዑካን ቡድኑ ዛሬ ማታ አዲስ አበባ የሚገባ ሲኾን በአዲስ አበባ በሚኖረው የሦስት ቀናት ቆይታም ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታ ያላቸውን የማምረቻ ቦታዎችን ይጎበኛል ነው የተባለው። በሚመለከታቸው የኢትዮጵያ ባለድርሻ መሥሪያ ቤቶች በኢትዮጵያ ስላሉት ምቹ የኢንቨስትመንት እና የንግድ አማራጮች ለባለሃብቶቹ ገለፃ የሚደረግበት የኢትዮ-ሳዑዲ አረቢያ የቢዝነስ የምክክር መድረክም እንደሚካሄድ አብራርተዋል።
የልዑካን ቡድኑ በግብርና፣ በማዕድን ዘርፍ፣ በቱሪዝም፣ በኃይል አቅርቦት፣ በትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ እንዲሁም በሌሎች ቁልፍ ኢኮኖሚያዊ ዘርፎች ያሉትን እድሎች ለመገንዘብ እንደሚፈልግም ቃል አቀባዩ ገልጸዋል። የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በማኅበራዊ ትስስር ገጹ እንዳለው በኢትዮጵያ የንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት እና በሳዑዲ አረቢያ አቻው መካከል የመግባቢያ ስምምነት ይፈረማል ተብሎም ይጠበቃል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
